በምስራቅ ቦረና ዞን በክልላዊና ሀገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች ሽልማትና እውቅና ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ቦረና ዞን በክልላዊና ሀገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች ሽልማትና እውቅና ተሰጠ

ነገሌ ቦረና ፤ ጥቅምት 3/2018 (ኢዜአ)፡- በምስራቅ ቦረና ዞን በ2017 ትምህርት ዘመን በክልላዊና ሀገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች ሽልማትና እውቅና ተሰጠ ።
በአገር አቀፍ ፈተናው የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ አስተዋጾ ላደረጉ መምህራንና ትምህርት ቤቶችም ሽልማትና እውቅና ተሰጥቷል፡፡
የምስራቅ ቦረና ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ ዮናስ በሪሶ በስነ ስርአቱ ላይ እንዳሉት በዞኑ በ12 ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ለመጀመሪያ ጊዜ 573 ነጥብ ተመዝግቧል፡፡
በመምህራን አቅም ግንባታ፣ በትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻል፣ በዲጂታል ቤተመጻህትና በትምህርት አቀራረብ ዘዴ መሻሻል ላይ በትኩረት መሰራቱ ለውጤቱ መመዝገብ ከፍተኛ አስተዋጾ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡
በዞኑ ለብሄራዊ ፈተና ከተቀመጡ ተማሪዎች ውስጥ 108ቱ የከፍተኛ ትምህርት የመግቢያ ውጤት ማስመዝገባቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡት መካከል 76ቱ የነገሌ ቦረና ከተማ ኢፋ ቦሩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ናቸው ብለዋል፡፡
የምስራቅ ቦረና ዞን አስተዳደር ተወካይ አቶ መሀመድ ኑራ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ለ6ኛ፣ ለ8ኛና ለ12 ክፍል 14 ተማሪዎች የገንዘብ ሽልማትና ሜዳሊያ መሰጠቱን ተናግረዋል።
አቶ ዮናስ አክለውም ለውጤቱ እገዛ ያደረጉ ስምንት መምህራን፣ ሰባት ትምህርት ቤቶችና አንድ ወረዳ አስተዳደር የዋንጫ ሽልማትና የእውቅና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡
የዞኑ አስተዳደር ህዝቡን በማስተባበር የትምህርት ስብራትን ለመጠገንና ጥራቱንም ለማሻሻል እየተሰራ ነው ብለዋል።
በትምህርት ስራው ግንባር ቀደም በመሆን ሜዳሊያ ተሸላሚ ከሆኑት መምህራን መካከል መምህር እውነቱ ማሞ የእውቅና ሽልማቱ የበለጠ ለመስራት እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።
በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጠንክረው እንደሚሰሩ አመላክተዋል።
ከተሸላሚ ተማሪዎች መካከል ተማሪ ገልገሎ ጉፋ የሜዳሊያና የገንብ ሽልማቱ በቀጣይም ጠንክሮ በማጥናት ከፍተኛ ውጤት ለማምጣት ብርታት እንደሆነለት ገልፅዋል።