ሠንደቅ ዓላማችንን በክብር ለትውልድ ለማስተላለፍ በሕብረ ብሔራዊ አንድነት ተግተን መስራት አለብን - ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ሠንደቅ ዓላማችንን በክብር ለትውልድ ለማስተላለፍ በሕብረ ብሔራዊ አንድነት ተግተን መስራት አለብን - ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር)

ቦንጋ/ወላይታ ሶዶ/ወልቂጤ፤ ጥቅምት 3/2018(ኢዜአ)፡- ሠንደቅ ዓላማችንን በክብር ለትውልድ ለማስተላለፍ በሕብረ ብሔራዊ አንድነት ተግተን መስራት አለብን ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።
18ኛው የሠንደቅ ዓላም ቀን በቦንጋ፣ በወላይታ ሶዶና ወልቂጤ ከተሞች በድምቀት ተከብሯል።
በቦንጋ በተከበረው በዓል ላይ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረ ሰቦችና ሕዝቦች ህብር መገለጫ የሆነውን ሠንደቅ ዓላማን በክብር መጠበቅ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በቀደምት አያቶቻችን አኩሪ ገድል ተጠብቆ የቆየውን ሠንደቅ ዓላማችንን በክብር ለትውልድ ለማስተላለፍ በሕብረ ብሔራዊ አንድነት ተግተን መሠራት አለብን ብለዋል።
የቀኑ መከበር ለሠንደቅ ዓላማ መስዋእትነት የከፈሉ ጀግኖችን ለማሠብና ለትውልዱ ለማስተላለፍ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የገለጹት ደግሞ የካፋ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ግርማ ደፋር ናቸው።
ሁሉም ዜጋ በተሠማራበት መስክ ሕዝቡን በታማኝነትና በቅንነት ለማገልገል በየዓመቱ ቃሉን የሚያድስበት መሆኑንም አመልክተዋል።
ሠንደቅ ዓላማ ክብርና መለያችን ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ፖሊስ አባል ኮማንደር በድሩ ማሞ ናቸው።
ቀደምት አያቶቻችን በክብር ያስረከቡንን ሠንደቅ ዓላማ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ተግተን እንሠራለን ብለዋል።
በተመሳሳይ በዓሉ በወላይታ ሶዶ በተከበረበት ወቅት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ፤ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ጀግኖች አያቶች የሀገርን ነፃነት ያስከበሩበት ምልክት መሆኑን ተናግረዋል።
የዘንድሮው የሠንደቅ ዓላማ ቀን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተመረቀበት እንዲሁም ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶች በተጀመሩበት ወቅት መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው አውስተው፤ ይህም የስኬቶቻችን ከፍታ ማሳያ ነው ብለዋል።
በርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተመስገን ጌታቸው፤ ሠንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ነው ብለዋል።
ሁላችንም በየተሠማራንበት ጠንክረን በመስራት የህዳሴ ግድብን እንዳሳካን ሁሉ ሌሎችንም የጋራ ፕሮጀክቶች በመፈፀም ደምቀን ለመታየት ትጋታችንን አጠናከረን መቀጠል አለብን ሲሉ ተናግረዋል።
በርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት የስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ዳይሬክተር አሠለፈች መብራቱ ፤ ሠንደቅ ዓላማ ከኢትዮጵያዊያን አልፎ ለሌሎች አፍሪካዊያንም የከፍታ ዘመን ማሳያ ዓርማ ነው ብለዋል።
ይህንን ደግሞ ህዝቡን በታማኝነትና በሐቀኝነት በማገልገል እንዲሁም በሁሉም ዘርፎች መልካም አስተዳደርን በማስፈን የሠንደቅ ዓላማን ክብር በተግባር ለመግለጽ እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዓሉ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተከበረበት ወቅት የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ መነቴ ሙንዲኖ ፤ ጀግኖች አያቶቻችን የነፃነት ምልክት የሆነውን ሠንደቅ ዓላማ ለአዲሱ ትውልድ ማስረከባቸውን ተናግረዋል።
ትውልዱም አብሮነቱንና ሀገራዊ አንድነቱን በማጠናከርና ልማትን በማፋጠን ኢትዮጵያን ከፍ የማድረግ አደራውን ማጠናከር አለበት ብለዋል።