ቀጥታ፡

የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ቀድሞ መከላከልና በራስ አቅም ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል የተቀናጀ አቅም እየተገነባ ነው

ሰመራ፤ ጥቅምት 3/2018(ኢዜአ)፦ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ቀድሞ መከላከልና በራስ አቅም ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል የተቀናጀ አቅም እየተገነባ መሆኑን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሸነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) ገለጹ።

ዓለም አቀፍ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ቀን "ለአደጋ ስጋት አይበገሬነት ግንባታ ትኩረት እንስጥ" በሚል መሪ ሃሳብ በአፋር ክልል በሰመራ ከተማ ተከብሯል።


 

በሁነቱ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሸነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር)፤ አደጋዎችን ለመከላከልና በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት በሁሉም ረገድ ዝግጁ መሆን ይገባል ብለዋል።

በተለይም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ምጣኔ ሃብት መገንባት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።


 

በተፈጥሮ የሚመጡ አደጋዎችን ቀድሞ የመከላከልና በራስ አቅም ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል የተቀናጀ አቅም መፍጠር እንደሚገባ አንስተው ለዚህም ዘላቂና የተቀናጀ አሰራር መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አክሊሉ ታደሰ፤ በተለይም የግብርና ልማት ስራዎችን በማስፋትና ምርታማነትን በማሳደግ ለአደጋዎች ጥንቃቄና ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም መገንባት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የቤተሰብ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና ሀገራዊ የኢኮኖሚ አቅምን በማሳደግ የምግብ ሉአላዊነትን ማረጋገጥ የጋራ አጀንዳ ሆኖ በተጠናከረ መልኩ መቀጠል አንዳለበትም አስገንዝበዋል።


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የአፋር ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ ኀላፊ አሊ መሐመድ፤ በክልሉ የሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን ቀድሞ የመከላከልና ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅም ለመፍጠር እየተሰራ ነው ብለዋል።

የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ የአደጋ ተጋላጭነትን የመቀነስ ስትራቴጂና ምርታማነትን የማሳደግ ስራም እንዲሁ።

በመርሃ ግብሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ(ዶ/ር)፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የአደጋ ስጋት አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም