ቀጥታ፡

ብሔራዊ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ኅብረብሄራዊ አንድነት እንዲጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2018(ኢዜአ)፦ ብሔራዊ የወጣቶች ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ኅብረብሄራዊ አንድነት እንዲጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ ገለጹ።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ብሔራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለያዩ መስኮች የኀብረተሰቡን ተጠቃሚነት ከፍ ያደረጉ ውጤቶች እየተገኘበት ነው።

በአቅመ ደካሞች ቤት እድሳትና ግንባታ፣ የጤና ምርመራና ህክምና፣ በትራፊክ አገልግሎት፣ በማዕድ ማጋራትና ሌሎች ዘርፎች በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

ለውጡን ተከትሎ ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰጠው ትኩረት ትልልቅ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ማስቻሉን ጠቅሰው በኀብረተሰቡ ዘንድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህል እየሆነ መምጣቱንም አንስተዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከኢኮኖሚ ጠቀሜታዎች ባሻገር የእርስ በእርስ ትስስር እንዲጎለብት አወንታዊ ሚና እየተጫወተ ነውም ብለዋል።

በተለይም ብሔራዊ የወጣቶች ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ኅብረብሄራዊ አንድነት እንዲጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

አንዱ የሌላውን እሴት እና ባህል እንዲያውቅ በማድረግ የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲጠናከር በማድረግ በኩል የላቀ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ዘላቂ ለማድረግ በአሰራር የማስደገፍ ሥራ በትኩረት እየተከናዋነ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ደኤታዋ ብሄራዊ የበጎ ፈቃድ ፖሊሲን ሥራ ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ፖሊሲው አስፈላጊው ግበዓት ከተሟላለት በኋላ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ሥራ ላይ እንደሚውልም አብራርተዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ውጤታማነት ለማሳደግ በቴክኖሎጂ በታገዘ አሠራር የማስደገፍ ጉዳይ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን አመልክተዋል።

በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጠቀሜታዎች ባለፈ ለጥቅል ሀገራዊ ምርት ያለውን አስተዋጽኦ መለካት የሚያስችል መስፈርት እየተዘጋጀ መሆኑንም ገልጸዋል።

መስፈርቱን ለማዘጋጀት የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎች ተቀምሮ በግብዓትነት መወሰዱን ጠቁመው በዘርፉ የተሻለ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ዓይነተኛ ሚና እንዳለውም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም