ቀጥታ፡

ሰንደቅ ዓላማ የሀገር አንድነት ማስጠበቂያ ብሔራዊ ዓርማ ነው

አምቦ/ ነቀምቴ ፤ ጥቅምት 3/2018(ኢዜአ)፡- ሰንደቅ ዓላማ የአገር አንድነት ማስጠበቂያ ብሔራዊ ዓርማና የነጻነታችን  ምልክት ነው ሲሉ የሆሚቾ አሙኒሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ የስራ አመራሮች እና ሰራተኞች ተናገሩ።

18ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የኢንዱስትሪው ሰራተኞችና አመራሮች በተገኙበት ተከብሯል።

በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን የሆሚቾ አሙኒሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ዋና ስራ አስኪያጅ ኮሎኔል ስለሺ ነገራ፣ ሰንደቅ ዓላማ የነጻነት ምልክት ነው ብለዋል።

የሰንደቅ ዓላማ ቀን ስናከብር ለሀገር አንድነት እና ሉዓላዊነት ዋጋ የከፈሉትን በማሰብ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ነጻነት ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።

የዛሬው ትውልድም የቀደምት አያቶች ፈለግ ተከትሎ የሀገር ሉዓላዊነት እና አንድነትን ለማስጠበቅ ከፊት መሰለፍ አለበት ሲሉም ተናግረዋል።

ከበዓሉ ተሳታፊዎች  ሌተናል ኮሎኔል ጌቱ ብርሃኑ በበኩላቸው ሰንደቅ ዓላማ የሀገር አንድነት ማስጠበቂያ ብሔራዊ አርማ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ቀደምት ጀግኖች አባቶች ሀገርን በክብር  ያወረሱን ለሰንደቅ ዓላማ ባላቸው ፍቅር  መሆኑን ጠቅሰው፤  የዛሬው ትውልድም ለዚህ በጎ ዓላማ መቆም አለበት ብለዋል።

ሀምሳ አለቃ አዲሱ ጉዲና፣ ለሰንደቅ ዓላማ ክብር እና ለሀገር ሉዓላዊነት የሚጠበቅባቸውን መሰዋእትነት ለመክፈል ምንጊዜም ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ምክትል አስር አለቃ ላቀች ሙሉዓለም  ወታደር በጀግንነት ወጥቶ ለሀገሩ ዳር ድንበር መስዋትነት የሚከፍለው ለሰንደቅ ዓላማ በመታመኑ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ለስንደቅ ዓላማ ክብር ሁሉም ዘብ መቆም አለበት ነው ያሉት።

በተመሳሳይ በነቀምቴ ከተማ የሰንደቅ ዓላማ ቀን አካባበር ላይ የተገኙት የነቀምቴ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ መሰረት ታደሰ እንደተናገሩት ሰንደቅ ዓላማ የአንድ ሀገር መገለጫ ነው ብለዋል።

የሀገርን ክብር እና ሉዓላዊነት ለማስከበር ቀደምት አባቶች ብዙ ዋጋ ከፍለዋል ያሉት አፈ ጉባኤዋ አሁን ያለው ትውልድም በልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ሀገር ወዳድነቱን ማረጋገጥ አለበት ብለዋል።

የነቀምቴ ከተማ ከንቲባ ተወካይ ረዳት ፕሮፌሰር መላኩ ጌታሁን በበኩላቸው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ስናከብር ሀገራችን የጀመረችውን የልማት ስራዎች በመደገፍ ለውጤታማነቱ በመረባረብ መሆን አለበት ሲሉ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም