ቀጥታ፡

ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ተረፈ ምርቶችን ወደ ሐብት በመቀየር ውጤታማ እየሆኑ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2018 (ኢዜአ)፡- ተረፈ ምርቶችን ወደ ሐብት በመቀየር ገቢ ከማመንጨት ባለፈ በአካባቢ ጥበቃ እና በስራ ዕድል ፈጠራ ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ገለጹ። 

በኢትዮጵያ በቅርቡ ብሔራዊ የሰርኩላር ኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ ይፋ የተደረገ ሲሆን ቆሻሻን መልሶ መጠቀምን ማስፋፋት፣ ለአካባቢ ተስማሚ ኢንዱስትሪዎችን መገንባት እና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ላይ የተመሠረቱ የሥራ ዕድሎችን ማስፋት ከዋና ዓላማዎች መካከል  ይጠቀሳሉ።

የአካበቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ እንደተናገሩት ለፍኖተ ካርታው  ውጤታማነት  የግል ዘርፉ ተሳትፎ የጎላ ነው።


 

ፍኖተ ካርታው ጽዱ ኢትዮጵያን ከማሳካት አንጻር የግሉ ዘርፍ ትልቁን ድርሻ እንዲወጣ የሚያስችል ነው ብለዋል።

የግሉ ዘርፍ የሚያስፈልገውን የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂና ሌሎች ድጋፎች  ያካተተ የተቀናጀ ስርዓት የሚዘረጋ መሆኑንም ተናግረዋል። 

ብሔራዊ የሰርኩላር ኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ ግቦችን ከማሳካት አንጻር ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ተረፈ ምርቶችን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ለአካባቢ ተስማሚና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ምርቶችን በማምረት  የጀመሩት ሥራ ምሳሌ ሆኖ የሚቀርብ ነው።

ወጣት ሚካኤል ኃይሌ ጥቅም ላይ የዋሉ ወረቀቶችን በመሰብሰብና መልሶ በመጠቀም የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ላይ እንደሚገኝ ይናገራል።


 

ምርቶቹም ለተቋማት ማስታወቂያ፣ ለጌጣጌጥ፣ ለስጦታና ለሌሎች አገልግሎቶች እየዋሉ መሆኑን ጠቁሞ የቆሻሻ አሰባሰብ ሂደቱን ከማህበረሰቡ ጋር በማስተሳሰር የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልጿል፡፡

ከየተቋማቱ የሚጣሉ ወረቀቶችን ለሚሰበስቡ ለበርካታ የጽዳት ሠራተኞችና ሴቶች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸውም አስረድቷል።

ወጣት ኢያሱ መዝገቡ የሙዝ ልጣጭን ከሌሎች ግብዓቶች ጋር በመጠቀም ለቤትና ቢሮ ቁሳቁሶች፣ ለጫማ እንዲሁም ለተለያዩ የቆዳ ምርቶች የሚውል አካባቢን የማይጎዳ ቀለም እያመረተ መሆኑን ገልፅዋል።


 

የእንጨት ተረፈ ምርቶችን በመጠቀም በውስጡ የሚገኘውን መርዛማ ጋዝ በማውጣት ለጤና የማይጎዳ የከሰል ምርት እያመረተ እንደሚገኝ የተናገረው ደግሞ ወጣት ኢዮብ አለሙ ነው፡፡

ምርቱ ከእንጨት ተረፈ ምርት የሚመረት በመሆኑ የደን ጭፍጨፋን በመከላከል ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጿል። 


 

ይህም የሀገሪቱን የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር እና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ሥራዎችን በመደገፍ ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አመልክቷል። 

ወጣቶቹ እንዳሉትም በቀጣይም ምርቶቻቸውን በስፋት በማምረት የሥራ ዕድል ፈጠራን ይበልጥ ለማስፋፋት ማቀዳቸውን ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም