ቀጥታ፡

ሠንደቅ ዓላማ መላው ኢትዮጵያውያንን ለጋራ ዓላማ የሚያሰባስብ ዓርማ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2018 (ኢዜአ)፡- ሠንደቅ ዓላማችን መላው ኢትዮጵያውያንን ለጋራ ዓላማ የሚያሰባስብ የማንነት መገለጫ ዓርማ ነው ሲሉ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ ገለጹ።

አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ 18ኛውን የሠንደቅ ዓላማ ቀን "ሰንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብስራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ" በሚል መሪ ሐሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል፡፡


 

በዚሁ ወቅት የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ሀገርን ከወራሪዎች ለመከላከልና ነጻነትን ለማስጠበቅ ሲደረግ የነበረው ተጋድሎ ምልክት መሆኑን አስገንዝበዋል።

የመረጃና ደኅንነት ተቋሙ አባላትም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም፣ ሉዓላዊነትና ክብር ለማስጠበቅ በሚያደርጉት ስምሪት የሠንደቅ ዓላማውን ትልቅ አደራ በልባቸው በመያዝ በከፍተኛ የሀገር ፍቅር መንፈስ እስከ መስዋዕትነት ድረስ ዋጋ ይከፍላሉ ብለዋል፡፡


 

ሠንደቅ ዓላማው መላው ኢትዮጵያውያንን ለጋራ ዓላማ የሚያሰባስብ የማንነት መገለጫ ዓርማ ነው ማለታቸውን አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ለኢዜአ በላከው መረጃ አመላክቷል።

ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተወጣጡትና በኅብረ-ብሔራዊ ስብጥር ለአንድ ሀገራዊ ዓላማ የተሰለፉት የተቋሙ አባላትም፤ በሠንደቅ ዓላማው ጥላ ስር ሀገራዊ ደኅንነትን የማረጋገጥ ተልዕኮን በላቀ መንፈስ የሚወጡ መሆኑን አስታውቀዋል።

በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በተከበረው 18ኛው የሠንደቅ ዓላማ ቀን የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮችና አባላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም