የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ሀገር የመገንባት አቅም የሚጎለብትበት የማንሠራራት ጉዞ ዓርማ ነው - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ሀገር የመገንባት አቅም የሚጎለብትበት የማንሠራራት ጉዞ ዓርማ ነው - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ፈተናዎችን በጽናት በመሻገር አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ሀገር የመገንባት አቅም የሚጎለብትበት የማንሰራራት ጉዞ ዓርማ መሆኑን የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
18ኛው የሠንደቅ ዓላማ ቀን ’’ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብስራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነትና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ’’ በሚል መሪ ሃሳብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተከብሯል።
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ወቅት፤ በሕገ መንግስቱና በሠንደቅ ዓላማ አዋጅ ድንጋጌ መሠረት የሠንደቅ ዓላማ ቀን በጥቅምት ወር መጀመሪያ ሳምንት ሰኞ በየዓመቱ ይከበራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ የዜጎች የብዝሃነት፣ የእኩልነትና የሕብረብሔራዊ አንድነት መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።
የሠንደቅ ዓላማ ቀንም ለሠንደቅ ዓላማችን ልንሰጠው የሚገባውን ክብር የምናድስበት፣ ቃልኪዳናችንን የምናጸናበትና ብሔራዊ የአርበኝነታችንን የምንቀሰቅስበት ነው ብለዋል።
ለሠንደቅ ዓላማ ቀን የተሰጠው መሪ ሀሳብም የዛሬውን ተግባር፣ የነገውን ምኞትና ትልም በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማም የውስጥና የውጭ ጠላቶች ሊሰብሩት የማይችሉት የሕብረብሔራዊ አንድነትና የሉዓላዊነት ምሽግ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ፈተናዎችን በጽናት በመሻገር አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ሀገር የመገንባት አቅም የሚጎለብትበትና ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪነት የሚታይበት የማንሰራራት ጎዞ ዓርማ መሆኑን አንስተዋል።
ሠንደቅ ዓላማችን በታሪክ ውጣ ውረዶች ውስጥ የጽናታችን ምልክት ነው ያሉት አፈጉባኤ ታገሠ፤ ዛሬም በዘላቂ ልማትና ብልጽግና ወደ ብሩህ የከፍታ ዘመን እየተሻገርን መሆኑን የምናውጅበት ነው ብለዋል።
በሠንደቅ ዓላማ ቀን አከባበር ላይ የታደሙ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ቅድመ አያቶች የታመኑላት የአሁኑ ትውልድም ለመጪው የሚያስረክባት ደማቅ ዓርማ መሆኗን ገልጸዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አራሬ ሞሲሳ፤ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ቅድመ አያቶች በደምና አጥንታቸው ጠብቀው ያቆዩት የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ዓርማ ምልክት ነው ብለዋል።
የአሁኑ ትውልድም ድህነትን ድል በመንሳት ለመጪው ትውልድ ዕድገትና ብልጽግናን ማውረስ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።
የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅና የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠላቸው ግዙፍ ፕሮክቶችም ዘመን ተሻጋሪ የሉዓላዊነት መገለጫና የኩራት ምንጭ በመሆናቸው የዘንድሮውን የሠንደቅ ዓላማ ቀን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አወቀ አምዛ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ቅድመ አያቶች የሀገርን ሉዓላዊ ነፃነትና ክብር በማስጠበቅ ለትውልድ ያሻገሯት ዓርማ ናት ብለዋል።
ሌላኛዋ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ከድጃ ሐሺም፤ የሠንደቅ ዓላማ ክብረ በዓል ታሪካችን የምናስታውስበት ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ የምንተጋበት ነው ብለዋል።