የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ አዲስ የትብብር እና የወዳጅነት ምዕራፍ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ አዲስ የትብብር እና የወዳጅነት ምዕራፍ

የአፍሪካ ቀንድ ለበርካታ አስርት ዓመታት በዕድሎችና ፈተናዎች መንታ መንገድ ላይ የቆመ ቀጣና ነው። የቀጣናው ሰፊ ዕድሎች በግጭት፣ በስጋት ተጋላጭነት እና በአለመተማመን ሲሸፈኑ ይታያል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በጋራ የትብብር መንፈስ ለጋራ ብልጽግና እያደረጉት ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደአዲስ እየጎለበት መጥቷል።
የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ስትራቴጂካዊ አካባቢ ሲሆን ከኤደን ባህረ ሰላጤ እስከ ታላቁ ስምጥ ሸለቆ ከ160 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መኖሪያም ነው። ቀጣናው ሰፊ የተፈጥሮ ሀብቶችና ለም የግብርና መሬት የታደለ እንዲሁም አፍሪካን ከመካከለኛው ምስራቅ ብሎም ከሌሎች ጋር የሚያስተሳስሩ የውሃ ኮሪደሮች ያሉበት ነው።
በቀጣናው ከትጥቅ ትግሎች እና ሽብርተኝነት የሚመነጩ የደህንነት ስጋቶች፣ ህገ-ወጥ ዝውውር፣ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ድርቆች፣ መፈናቀሎች፣ የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ፣ የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎችም የቀጣናውን ሀገራት አይበገሬነትና አቅም እየፈተኑት ይገኛሉ።
በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ጫናዎችና በየጊዜው የሚቀያየሩ የኃይል አሰላለፎች በቀጣናው የሚታዩ ፈተናዎችን የበለጠ አክብደውታል።
የአፍሪካ ቀንድ ከውስጣዊ ትብብር ይልቅ የውጭ አካላት ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚራኮቱበት ቀጣና በሚል የሚፈርጁትም አሉ። አሁን አሁን በቀጣናው ከሚስተዋሉ ችግሮች ለየት ያለ አዲስ ነገር መታየትም መሰማትም እየጀመረ መጥቷል።
በቀጣናው የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቀየር ትብብርና ትስስር፣ ለመከባበርና የሰላም መንገድን ለመከተል ያሉ ፍላጎቶች እያደጉ መጥተዋል። ቀጣናዊ ትስስር የሚለው አጀንዳ ተገቢው ትኩረት እየተሰጠው መሆኑም እየተስተዋለ ይገኛል።
የቀጣናው ሀገራት ወደ ውስጣቸው በመመልከት ፈተናዎችን በስክነት የመፍታት መንገድን መከተል ጀምረዋል። ለአፍሪካ ፈተናዎች አፍሪካዊ መፍትሄዎች የሚለውን መርህ ሀገራት እየገዙት ያለ አህጉራዊ ማዕቀፍ እና እሳቤ ሆኗል።
ለመሰረተ ልማት፣ ለኢነርጂ ትስስሮችና ለድንበር ተሻጋሪ ንግድ እየፈሰሰ ያለው መዋዕለ ንዋይ ቀጣናው የበለጠ እንዲተሳሰር መልካም አጋጣሚ ፈጥረዋል። ኢትዮጵያ በቅርቡ ያስመረቀችው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቀጣናዊ ትብብርና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ተምሳሌት ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ለቀጣናው ገበያዎች አዳዲስ እድሎችን ይዞ መጥቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዲፕሎማሲ ሁነቶች ሀገራት ለውይይት ያላቸውን ዝግጁነት የሚያመላክት ነው።
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲም ቅድሚያ ለጎረቤት የሚሰጥ ነው። ከቀጣናው ሀገራት ጋር በጋራ መልማትና ማደግ አበይት የፖሊሲው ምሰሶ ሆኖ በግልጽ ተቀምጧል።
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛው የሥራ ዘመን የ2018 የጋራ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር መንግስት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ቅድሚያ ለጎረቤት የሚለውን መርህ አጠናክሮ እንደሚቀል ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ዘርፈ ብዙ ትብብር ለመፍጠር ጥረት መደረጉንና ከጎረቤት ሀገራት ጋር ግጭት እንዳይፈጠር ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን አውስተዋል።
ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ የመሰረተ ልማት ስራዎች መከናወነቸውን ጠቅሰው በቀጣይነትም ኢኮኖሚያዊ ትብብርን የሚያጎለብቱ የመሰረተ ልማት ዝርጋታና የንግድ ልውውጥ እንዲጠናከሩ ይደረጋል ብለዋል።
በዚህ ረገድ መንግስት የጀመራቸውን ትብብሮች አጠናክሮ እንደሚቀጭልና በአካባቢያችን ሰላምን ለማረጋገጥ አለመግባባቶችን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት አበክሮ እንደሚሰራም ነው ፕሬዚዳንቱ የገለጹት።
በቀጣናው እየተቀየረ ባለው ምህዳር ውስጥ የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ትብብር በቅርቡ ከታዩ መልካም የዲፕሎማሲ ጉዳዮች መካከል የሚጠቀስ ነው። ሁለቱ ሀገራት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የጋራ ፍላጎትና የጋራ ብልጽግናን መሰረት ባደረገ መልኩ ትብብራቸውን ለማጠናከር እየሰሩ ይገኛሉ።
የሶማሊያ ፌደራል ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ ትናንት ጥቅምት 2/2018ዓም በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸውና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ይታወሳል።
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ውይይት በቅርብ ጊዜ በሀገራቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል የተደረጉ ውይይቶች ቀጣይ አካል ሆኖ ሊወሰድ የሚችል ሲሆን በታህሣሥ 2017 ዓ.ም ላይ በቱርኪዬ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን አሸማጋይነት የተደረገው የአንካራ ስምምነት በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት የቀረፈ ስምምነት ነበር።
ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላምና ትብብርን የሚያጎለብት፣ የሀገራቱን ሕዝቦች ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክር፣ ለቀጣናው ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና የሚበጅ ታሪካዊ ስምምነት እንደነበርም ይታወሳል።
የአንካራ ስምምነት ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ ለምታደርገው ጥረት በር ከፋች ሆኗል። በዚህም የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት መሻት ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንዲያገኝም አስችሏል። በዚህም የኢትዮጵያ የባህር በር የመሻት ጥያቄ ህጋዊ፣ ሞራላዊና ፖለቲካዊ መሰረት ያለው ነው።
ይህም ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ የዘርፉ ምሁራንም ስምምነቱ ከሁለቱ ሀገራት ባሻገር ለወዳጅ ሀገራት ጭምር ተስፋ የፈነጠቀ ክስተት ነው ሲሉም ገልጸውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ሶማሊያን ከአሸባሪዎች ለመከላከልና ሠላሟን ለማረጋገጥ ሲባል በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል አባላት በከፈሉት መስዋዕትነት ጭምር የተሳሰረ መሆኑን ነው የገለጹት። ኢትዮጵያ ለጋራ ሠላምና ልማት ከሶማሊያ ጋር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ አረጋግጠዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድም ለዚህ ሀቅ ጠንካራ እማኝነታቸውን ሰጥተው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለሀገሪቱ ሠላም መጠበቅ ለዓመታት የከፈለውን ዋጋ መቼም አይዘነጋም ሲሉ የሚገባውን ክብር መስጠታቸውም ይታወሳል።
ሶማሊያ የኢትዮጵያ እውነተኛ ወዳጅ ሆና ትቀጥላለች ሲሉም ማረጋገጣቸው እንዲሁ። ሁለቱ ሀገራት በቀጣይም ሠላምን ለማፅናት በሚያደርጉት ጥረት መንግሥታቸው ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረው ነበር። ከስምምነቱ በኋላ በሁለቱ ሀገራት መሪዎች መካከል የጉብኝት ልውውጦች ተደርገዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐሙድ በጥር ወር 2017 ዓ.ም ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ይታወሳል። ሀሰን ሼክ ማሃሙድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር መወያየታቸውና የጋራ መግለጫ ማውጣቸው አይዘነጋም።
በውይይቱ ሁለቱ ሀገራት በየሀገራቱ ያላቸው ሙሉ የዲፕሎማሲ ውክልና በመመለስ ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ነበረበት ለመመለስ እና ለማሻሻል ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። የሀገራቱ መሪዎች የዲፕሎማሲ ሚሲዮኖቻቸው በባለብዝሃ ወገንና በቀጣናዊ ፎረሞች ላይ የሀገራቱ የጋራ ፍላጎቶች ላይ በቅርበት መስራት እንዳለባቸውም አጽንኦት መስጠታቸው ይታወሳል።
መሪዎቹ ለቀጣናው መረጋጋት የሁለቱ ሀገራት በጋራ መተማመንና መከባበር ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ትብብር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ለማሻሻል፣ የጋራ መግባባት ለመፍጠርና የጋራ ግቦችን እውን ለማድረግ በትብብር ለመስራት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በተጨማሪም በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የጸጥታና ደህንነት ትብብራቸውን ለማጠናከር ቀጣይነት ያለው ስራ ማከናወን እንደሚያስፈልግም ተመላከቷል። በየጊዜው እያደገ የመጣውና አሳሳቢ የሆነው የታጠቁ ቡድኖች በቀጣናው ላይ የደቀኑት ስጋት በውይይቱ መነሳቱም ይታወሳል።
በተጨማሪም መሪዎቹ ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚ፣ ኢንቨስትመንት እና ንግድ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር መስራት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጠንካራ የኢኮኖሚ ትብብር በመፍጠር የንግድ ትስስራቸውን የሚያሳልጡ የመሰረተ ልማት መስመሮችን ለማስፋት እና የጋራ ብልጽግናቸውን ለማረጋገጥ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው በጋራ መግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
መሪዎቹ ለአንካራው ስምምነት ትግበራ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገልጸው ስምምነቱ ከሀገራቱ የወዳጅነት እና የአጋርነት መንፈስ የመነጨ እንደሆነም ተወስቷል። በስምምነቱ የተቀመጠውን የቴክኒክ ድርድሮች በፍጥነት እንዲጀመሩ ለማድረግ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን በጋራ መግለጫው መመላከቱም እንዲሁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የልዑካን ቡድናቸው በየካቲት ወር 2017 ሶማሊያን መጎብኘታቸው የሚታወስ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር ) በሶማሊያ ያደረጉትን ጉብኝት አስመልክቶ በወቅቱ በሰጡት ማብራሪያ ጉብኝቱ የሁለቱን ጎረቤት ሀገራት ትብብርና ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ በማድረግ ረገድ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው እንደሆነ አንስተው ነበር።
ጉብኝቱ ሀገራቱ ወደ አዲስ የትብብር እና የወዳጅነት ምዕራፍ እንደደረሱ የሚያመላክት መሆኑን ጠቁመው ቀደም ብሎ በተለያየ ደረጃ ሲደረጉ የነበሩ ውይይቶችና ጉብኝቶች የሀገራቱን ትብብር ይበልጥ መጠናከሩን የሚያሳዩ በተለይም በፀጥታው ዘርፍ እና በሰላም ማስከበር ኢትዮጵያ ያላትን ተሳትፎና የሀገራቱን ትብብር መልክ ያስያዙ መናቸውንም እንዲሁ።
የመሪዎቹ የጉብኝት ልውውጦች የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው እንዲሻሻል የሰጡትን ትኩረትና ያላቸውን የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንደሚያሳይም ተናግረው ነበር።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት፥ በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለፉት ጥቂት ወራት የነበራቸውን ገንቢ ውይይቶች ተከትሎ የመጣ እና የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ነበረበት የመመለስን ስራ የሚያጠናክር መሆኑን የሀገራቱ መንግስታት የጋራ አቋም መግለጫ አመልክቷል።
የሁለቱ መሪዎች የሀገራቱን የጋራ ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ ትብብራቸውን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሀገራቱ ህዝቦች ጥልቅ የሆነ ታሪካዊ ግንኙነትና የሚያስተሳስራቸው የጋራ ድንበር እንዳላቸው ያወሳው መግለጫው፥ በዚህ ረገድም በዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትብብር መተማመንን መገንባት ወሳኝ መሆኑ እንደታመነበትም ተመላክቷል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለቀጣናዊ መረጋጋት እና ብልጽግናን እውን የማድረግ የጋራ ራዕይ ያላቸው ሀገራት መሆናቸውንም አመላክቷል።
በዚህ ረገድ የሀገራቱ መሪዎች ዘላቂ ልማትን የሚያረጋግጡ፣ የኢኮኖሚ ትስስርን የሚያሳልጡና የህዝብ-ለህዝብ ትስስርን የሚያጠናክሩ ስትራቴጂካዊ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለመተግበር ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ነው መግለጫው ያመለከተው።
በተጨማሪም መሪዎቹ በአንካራ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ የቴክኒክ ውይይት መጀመሩ መልካም የሚባል መሆኑንና ይህም ሀገራቱ ገንቢ ውይይትና ትብብር ለመፍጠር ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት የሚያሳይ መሆኑ ተመላክቷል።
መሪዎቹ በሶማሊያ ብሔራዊ ወታደራዊ ኃይል እና በኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አዛዦች መካከል የደህንነት ትብብር ለማጠናከር ብሎም ቀጣናዊ መረጋጋትን ለማስፈን ለደረሱበት የጋራ መግባባት እውቅና ሰጥተዋል።
ሁለቱ ወገኖች የጋራ ፍላጎታቸውን በማራመድ፣ ሰላም እና ደህንነትን በማረጋገጥ እንዲሁም የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ይበልጥ በማጠናከር ዜጎቻቸውን አልፈውም የአፍሪካ ቀንድን ተጠቃሚ ለማድረግ በጋራ እንደሚሰሩ መግለጻቸውም በመግለጫው ተንጸባርቋል።
የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼህ መሃሙድ በጳጉሜን ወር 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ በነበራቸው ጉብኝት በቀጣናችን ፀጥታ እና መረጋጋት ብሎም ልማትን ለማረጋገጥ ያለንን ፅኑ አቋም በድጋሜ አረጋግጠናል ሲሉ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መልካም ጉርብትና ትስስር ማደግ ለሀገራቱ መጻኢ ጊዜ አጋርነት መሰረትን የሚጥል በጎ ጅማሮ ነው። ከሀገራቱ ባለፈ ለአፍሪካ ቀንድ መልካምና ተስፋ ሰጪ ብስራት ነው ማለት ይቻላል።
የሁለቱ ሀገራት የዲፕሎማሲ፣ ኢኮኖሚያዊና የደህንነት ትብብር ማደግ ለቀጣናው መረጋጋት፣ ንግድ ትስስር መጠናከር እና የጋራ እድገትን የሚያሳልጥ ነው። የሀገራቱ ትስስር መጠናከር እንደ መልካም የዲፕሎማሲ እርምጃ የሚታይ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት፣ አንድነት እና የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ ስትራቴጂካዊ እድል ይዞ መጥቷል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐሙድ በቅርቡ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምርቃት ላይ ያደረጉት ንግግርም ይህንኑ ሀሳብ የሚያጠናክር ነው። በዚህ ወቅትም የግድቡ ተገንብቶ መመረቅ ለቀጣናው ኩራት መሆኑን ማንሳታቸው ይታወሳል።
የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ እየሄደችበት ላለው የብልጽግና ጉዞ ወሳኝ መሆኑንና ፕሮጀክቱ ከአንድ ግድብነት ያለፈ መሆኑንም ተናግረዋል። በንግግራቸውም የሶማሊያ ፍላጎት በትብብር መልማትና ማደግ መሆኑን አሳውቀዋል።
ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ያከናወነችው ሥራ ትልቅ ታሪክ መሆኑን በመግለጽ፤ ለሀገራቸው የሚጠቅም ተነሳሽነት መሆኑንም ነው ያስረዱት።
የትብብሩ እድገት ለመሰረተ ልማት ትብብር፣ ለድንበር ተሻጋሪ የንግድ ልውውጥና የደህንነት ስጋቶች እንዲሁም አየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ ለጋራ ፈተናዎች በተቀናጀ መልኩ ምላሽ ለመስጠት በር ይከፍታል።
የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ለአፍሪካ እና ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ትስስር ግቦች መሳካት ትልቅ ድርሻ ይወጣል።