ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የተመዘገቡ ድሎችን በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል በአንድነት መሥራት ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የተመዘገቡ ድሎችን በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል በአንድነት መሥራት እንደሚገባ የብልጽግና ፓርቲ አመራር አባላት ገለጹ።

18ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት አመራር እና ሰራተኞች በተገኙበት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።


 

የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የአስተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ ሚኒስትር ዴኤታ ብርሃኑ ፈይሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የቀደሙ አባቶች በከፈሉት የህይወት መስዋዕትነት የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ክብር ከፍ እንዲል አድርገዋል።

አትሌቶቻችንም የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ በኩራት እንዲውለበለብ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን አንስተዋል።

የአሁኑ ትውልድ የአባቶች አደራ አለበት ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ የተነደፉ ኢኒሼቲቮች ላይ በመሳተፍ አደራውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አንድነትን በማጎልበት የተጀመሩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ከግብ ለማድረስ በጋራ መስራትን ማጠናከር እንደሚገባም ጠቁመዋል።


 

በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የዲሞክራሲ ባህል ግንባታና የምርጫ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አሸብር ታደሰ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሰንደቅ ዓላማን ማክበራችን የሚገለጸው በሥራ ነው፤ ለዚህም የሚመጥን ተግባር ለማከናወን መትጋት አለብን ነው ያሉት።

በአንድነት ተቀራርበን ከሰራን አባቶች የሰጡንን ሀገር የማሻገር አደራ መወጣት እንችላለን ሲሉም ተናግረዋል።

ሀገር ተረካቢው ትውልድ የዳበረ የሀገር ፍቅር እንዲኖረው ከታች ጀምሮ ትውልድን የማነጽ ኃላፊነት የኛ ሊሆን ይገባል ብለዋል።


 

በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ነብዩ ስሁል እንዳሉት የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ባሳካንበት ማግስት የሰንደቅ ዓላማ ቀን መከበሩ ልዩ ገጽታ ያላብሰዋል።

የኢትዮጵያ ስም እና ተሰሚነት እየጎላ መምጣቱን ገልጸው በኢትዮጵያ የተመዘገቡ ስኬቶችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከትውልዱ ብዙ ሥራ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።


 

የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ምክትል ፕሬዝዳንት አባንግ ኩመዳን በበኩሏ፤ አባቶች በከፈሉት መስዋዕትነት ሉዓላዊት ሀገር አስረክበውናል እኛ ደግሞ በየተሰማራንበት የሙያ መስክ ኃላፊነታችንን በመወጣት ለሀገርና ለሰንደቅ ዓላማ ያለንን ክብር በተግባር ማረጋገጥ ይገባናል ብላለች።

18ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን "ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ" በሚል መሪ ሃሳብ በመላ ሀገሪቱ በተለያዩ ኹነቶች ተከብሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም