በባሕርዳር እየተከናወኑ የሚገኙ አበረታች የልማት ተግባራት የተጀመረውን የማንሰራራት ጉዞ ለማሳካት የሚያግዙ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በባሕርዳር እየተከናወኑ የሚገኙ አበረታች የልማት ተግባራት የተጀመረውን የማንሰራራት ጉዞ ለማሳካት የሚያግዙ ናቸው

ባሕርዳር፤ ጥቅምት 3/2018 (ኢዜአ)፡- በባሕር ዳር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ አበረታች የልማት ተግባራት እንደሀገር የተጀመረውን የማንሰራራት ጉዞ ለማሳካት የሚያግዙ መሆናቸው ተመላከተ።
በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ የተመራ ቡድን በባሕርዳር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ተግባራትን ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
በዚህ ወቅት ከንቲባው አለማየሁ አሰፋ ፤ ኮሪደርን ጨምሮ ደረጃቸውን የጠበቁ የመንገድ መሰረተ ልማቶችና ወደ ጣና የሚያስገቡ መንገዶች፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫና ሌሎችንም የግንባታ ተግባራት ተዘዋውረው መመልከታቸውን ተናግረዋል።
በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ተግባራት ባሕር ዳርን ይበልጥ ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን የሚያስችላት መሆኑን ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማቱን ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር ጣናን ለጎብኚዎችና ለነዋሪዎች የመግለጥ ተግባር ከተማዋን ሳቢና ማራኪ እንድትሆን አድርጓታል ብለዋል።
እየተገነቡ የሚገኙት የልማት ተግባራት የሕዝብ ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ እንደሆኑ መገንዘባቸውን ጠቁመው፤ ይህም ሀገሪቱ ወደ ብልፅግና ለመሸጋገር የጀመረችውን ጉዞ ለማፋጠን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙ አበረታች የልማት ተግባራት የተጀመረውን የማንሰራራት ጉዞ ለማሳካት የሚያግዙ ናቸው ብለዋል።
አመራሩ ከሕብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ የከተማዋን እድገት ለማፋጠን እየተጋ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ያነሱት ከንቲባው፤ ከባሕርዳር ያገኙትን ልምድና ተሞክሮ በቢሾፍቱ በሚገኙ የኃይቅ ዳርቻዎች ተግባራዊ በማድረግ የከተማቸውን ዕድገት ለማፋጠን እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው፤ የባሕር ዳር ከተማን ዕድገት የሚያፋጥኑ የልማት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
የከተማዋን ሰላም በማፅናት የኮሪደር ልማት፣ የስማርት ሲቲ፣ ሰፋፊ የአስፋልት መንገዶች፣ የአረንጓዴና ሌሎች የልማት ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።
በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ የተመራው ቡድን እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ተግባራትን መመልከቱ የጋራ የልምድና ተሞክሮ ልውውጥ ለማድረግ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
በቀጣይም የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አመራሮች ወደ ቢሾፍቱ ከተማ አቅንተው በመጎብኘት ግንኙነቱንና ትስስሩን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩም አመልክተዋል።