ሀገራዊ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከፍ ባለ የሠንደቅ ዓላማ ክብርና ፍቅር እውን እንዲሆኑ ሙያዊ ሃላፊነታችንን እናጠናክራለን - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከፍ ባለ የሠንደቅ ዓላማ ክብርና ፍቅር እውን እንዲሆኑ ሙያዊ ሃላፊነታችንን እናጠናክራለን

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 3/2018 (ኢዜአ)፡-እንደ አገር የተያዙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከፍ ባለ የሠንደቅ ዓላማ ክብርና ፍቅር እውን እንዲሆኑ ሙያዊ ሃላፊነታቸውን እንደሚያጠናክሩ የኢዜአ አመራሮችና ሰራተኞች አረጋገጡ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራሮችና ሰራተኞች 18ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን''ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብስራት ለብሔራዊ አንድነታችን ሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ'' በሚል መሪ ሀሳብ በፓናል ውይይትና ሠንደቅ ዓላማ በመስቀል አክብረዋል።
አመራሮችና ሰራተኞቹ የሠንደቅ ዓላማ ቀንን ሲያከብሩ እንደ ሀገር የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ ከፍ ባለ የሰንደቅ ዓላማ ክብርና ፍቅር ሙያዊ ሃላፊነታቸውን በመወጣት መሆኑን አረጋግጠዋል።
ሠንደቅ ዓላማ ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ የገጠማቸውን ፈተናዎች በድል በማለፍ የሀገርን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ የደም መስዋዕትነት ከፍለው ያስገኙት የነጻነት አርማ መሆኑም ተነስቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፥ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለአፍሪካ ኩራት የሚሆኑ ግዙፍ አገራዊ ፕሮጀክቶችን እያከናወነች ባለችበት ጊዜ የሠንደቅ ዓላማ ክብርና ፍቅር የበለጠ ይጎላል ብለዋል።
እንደ አገር የተጀመሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን አንድነትን የበለጠ በማጠናከር ከግብ ለማድረስ ቃላችንን ማደስ አለብን ነው ያሉት።
እንደ አገር የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ስራዎች ወደ ኋላ እንዳይቀለበሱ የጋራ ርብርብ ማድረግ ወሳኝ መሆኑንም ነው ያነሱት።
በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የክልል ዴስክ ምክትል ዋና አዘጋጅ በለጠ አድነው፥ እንደ አገር በቀጣይ የተያዙ ትላልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶችን ከፍ ባለ የሠንደቅ ዓላማ ክብርና ፍቅር ለመፈጸም ሙያዊ ሃላፊነታችንን በትጋት እንወጣለን ብሏል።
በተለይም ከአገራዊ ለውጡ በኋላ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን የበለጠ በማጠናከር ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን እውን ማድረግ መቻላቸውን ያነሳው ደግሞ በኢዜአ የክልል ዴስክ ምክትል ዋና አዘጋጅ ሀብታሙ አክሊሉ ነው።
ይህም የአገርንና የሰንደቅ ዓላማን ክብር የበለጠ ከፍ የሚያደርግና በራስ የመፈጸም አቅምን ያሳየ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የክልል ግንኙነት ቡድን መሪ ዮሃንስ ወንድይራድ የውይይት መነሻ ሀሳብ ባቀረበበት ወቅት፥ ኢዜአ ብሄራዊ መግባባትና አገራዊ ገጽታ የመገንባት ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ነጋሲ አምባዬ በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ፥ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ በቀደምት አባቶች ደማቅ ታሪክ የተጻፈ ሰንደቅ ዓላማ ባለቤት ናቸው ብለዋል።
ትውልዱ ይህን የአባቶቹን አኩሪ ታሪክ ጠብቆ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ያሉ ዕድሎችን አሟጦ መጠቀም ይገባዋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ኩራት የሆኑ አኩሪ ታሪኮች ያላት አገር እንደመሆኗ ይህን ታሪክ ጠብቆ ማቆየትና የሰንደቅ ዓላማን ክብር ከፍ ማድረግ የሁሉም ሃላፊነት መሆኑንም ነው ያነሱት።