ቀጥታ፡

 የሰንደቅ ዓላማን ክብር አስጠብቆ ለትውልድ በማስተላለፍ ታሪካዊ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል-ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ

ጋምቤላ፤ ጥቅምት 3/2018 (ኢዜአ)፡- የህብረ ብሔራዊ አንድነት መገለጫ የሆነውን የሰንደቅ ዓላማችንን ክብር አስጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ታሪካዊ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።

’’ሰንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብስራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ህዳሴ’’ በሚል መሪ ሃሳብ 18ኛው የብሔራዊ ሰንደቅ ዓለማ ቀን በጋምቤላ ክልል በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።


 

ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ በክብረ በዓሉ ላይ ሰንደቅ ዓላማ በብዝሃነት ውስጥ ያለውን አንድነትንና ወንድማማችነትን ያስተሳሰረ ብሔራዊ ዓርማ መሆኑን ተናግረዋል።

ሰንደቅ ዓላማ ጀግኖች አባቶች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር የተዋደቁበት ህያው ምልክት ከመሆኑም ባለፈ የህዝቦች የአንድነት ቃል ኪዳን ዓርማ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

በመሆኑም ለሰንደቅ ዓለማችን ክብር ለተደረገውና እየተደረገ ላለው ተጋድሎ ተገቢውን እውቅና በመስጠት ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

በተለይም ዕለቱን ስናከብር ወጣቱ ትውልድ የሰንደቅ ዓላማ ምንነት፣ ክብርና ትርጓሜን ተገንዝቦ ከአባቶቹ የተረከበውን ታሪካዊ ኃላፊነት እንዲወጣ ለማስችል ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ሌሎች የልማት ስኬቶች በተመዘገቡበትና አዳዲስ ሜጋ ፕሮጀክቶች በተጀመሩበት ማግስት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሳይመን ሙን (ዶ/ር) በበኩላቸው ሰንደቅ ዓላማ የማንነታችንና የአንድነታችን መገለጫ ህብረ ብሔራዊ አርማችን ነው ሲሉ ገልጸዋል።


 

በመሆኑም ለብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማችን ልዩ ክብርና ፍቅር በማሳየት ሁለንተናዊ የልማትና የብልጽግና ጉዟችንን ልናጠናክር ይገባል ብለዋል።

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል በጡረታ የተገለሉት ኮሎኔል ኡዋር ኡቦንግ በሰጡት አስተያየት ሰንደቅ ዓላማችን የጀግንነትና የነፃነት ተጋድሎ ብሔራዊ ዓርማችን ነው ብለዋል። 


 

በዓሉ በየዓመቱ በዚህ መልኩ መከበሩ ትውልዱ ስለ ሰንደቅ ዓላማው ያለውን ክብርና ፍቅር እንዲያጠናክር የሚያደርግ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጋራ የማንነት መገለጫ ነው ያሉት ደግሞ ሌላዋ የበዓሉ ታዳሚ ወይዘሮ ካሰች ታፈሰ ናቸው።


 

በጋምቤላ ከተማና በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሰንደቅ ዓላማ ቀን በወታደራዊ የሰልፍ ትርዒት፣ በባህላዊ ጭፈራና በሌሎች ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም