ቀጥታ፡

የሠንደቅ ዓላማ ቀን ኢትዮጵያውያን የነገ ተስፋቸውን የሚያጸኑበት ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2018 (ኢዜአ)፡- የሠንደቅ ዓላማ ቀን ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ፍቅርና አንድነትን የሚያድሱበት የነገ ተስፋቸውን የሚያጸኑበት ነው ሲሉ  የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ። 

18ኛው የብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን "ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ" በሚል መሪ ሃሳብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተከብሯል። 


 

በሥነ-ስርዓቱ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት፣ ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፣ የመከላከያ ሠራዊት መኮንኖች፣ የሁለቱ ምክር ቤት አባላትና አባት አርበኞች ተገኝተዋል። 

በዚሁ ወቅት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፥ ሠንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አርማ የሉዓላዊነት መገለጫ ማህተም ነው ብለዋል። 

በየዓመቱ የሚከበረው የሠንደቅ ዓላማ ቀንም ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው ፍቅርና አንድነትን የሚያድሱበት የነገ ተስፋቸውን የሚያጸኑበት መሆኑን ተናግረዋል። 


 

የዘንድሮው 18ኛ የሠንደቅ ዓላማ ቀን ታላቁ የህዳሴ ግድብ በተጠናቀቀበት ማግስት መከበሩም የኢትዮጵያን የልማትና የከፍታ ዘመን የሚያመላክት በመሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል። 

ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ዓለም አቀፍ ከበሬታና ሞገስ ባገኘችበት፣ በግብርና ምርታማነትና ሰፋፊ የልማት መስኮች አኩሪ የሠንደቅ ዓላማን ክብር የሚያጎሉ ስኬቶች የተመዘገቡበት መሆኑን ገልጸዋል። 

ግንባታቸው የተጀመሩ የአፈር ማዳበሪያና የተፈጥሮ ጋዝ ፋብሪካ ግንባታም የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልጽግና በማሳለጥ የሀገርን የከፍታ ጉዞ የሚያረጋግጡ መሆናቸውን አስገንዝበዋል። 

በቀጣናው የጋራ ተጠቃሚነት እና ትብብር ላይ የተመሰረተውን ፍትሐዊ የባሕር በር የመጠቀም እና የማግኘት መብታችንን በሰላማዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እንዲሁም በሰጥቶ መቀበል መንገድ ማስከበራችን የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል። 

የሀገርን ሰላምና ሉዓላዊ ደኅንነት በጽናት እያስጠበቁ ለሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የክልል ጸጥታ ኃይሎችም ምስጋና አቅርበዋል። 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፥ በሕገ መንግስቱና የሠንደቅ ዓላማ አዋጅ መሠረት የሠንደቅ ዓላማ ቀን በየዓመቱ እንደሚከበር ገልጸዋል። 


 

የዘንድሮው "ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ" መሪ ሃሳብም የዛሬውን ስኬትና የቀጣዩን ህልም የሚያድስ መሆኑን ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማም የሕብረ ብሔራዊ አንድነት ማህተም የማንሰራራት ጉዞ የጽናት ምልክት መሆኑን አስገንዝበዋል። 

የብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በሠንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 863/2006 (እንደተሻሻለው) አንቀጽ 2 መሰረት በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ መጀመሪያ ሳምንት ሰኞ እንደሚከበር ተደንግጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም