ቀጥታ፡

ሰንደቅ ዓላማችን ጀግኖች አባቶች ወራሪዎችን በማሸነፍ በድል ያወረሱን የሉዓላዊነታችን መገለጫ ነው

ጂንካ፤ ወላይታ ስዶ ፤ ጥቅምት 3/2018 (ኢዜአ)፡- ሰንደቅ ዓላማችን ጀግኖች አባቶች ከወራሪዎች ጋር ተጋድለው በማሸነፍ በድል ያወረሱን የሉዓላዊነታችን መገለጫ ነው ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ተናገሩ።

18ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ''ሰንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብስራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነትና ለኢትዮጵያ ህዳሴ" በሚል መሪ ሀሳብ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ሶዶ ከተማ ተከብሯል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ሰንደቅ ዓላማ የመስቀል ስነ-ስርዓት ያከናወኑት የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ገብረ መስቀል ጫላ ባስተላለፉት መልዕክት ሰንደቅ ዓላማችን የነፃነታችን ምልክት ነው ብለዋል።

ሰንደቅ ዓላማችን ጀግኖች አባቶች ከወራሪዎች ተጋድለው በማሸነፍ በድል ያወረሱን የሉዓላዊነታችን መገለጫ ነው ብለዋል።

የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን እንደ ሀገር መላውን ህዝብ ያስተሳሰሩና የሀገሪቱን የመልማት ራዕይን ያሳኩ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶች በተመረቁበት ወቅት መከናወኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።


 

በወላይታ ሶዶ ከተማ በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ጽህፈት ቤት ቅጥር ግቢ በተካሄደው መርሃ ግብር የክልሉ መንግስት የስራ ኃላፊዎችና የመንግስት ሰራተኞች እንዲሁም የጸጥታ ኃይሎች የተገኙ ሲሆን ቃለ መሃላ የመግባት ስነ-ስርዓትም ተካሄዷል።

በተመሳሳይም የሰንደቅ ዓላማ ቀን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጂንካ ከተማም በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል።

ሰንደቅ አላማ  ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ህብረ-ብሔራዊነታቸውን ለማፅናት ቃል ኪዳን የገቡበት መሆኑን  የገለጹት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ ናችው።


 

ሰንደቅ አላማ አባቶች መስዋዕትነት በመክፈል ደማቅ ታሪክ የሰሩበት በመሆኑ የአሁኑ ትውልድም እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰሉ ብሔራዊ ኩራት የሆኑ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ታሪኩን ዳግም ፅፏል ብለዋል።

የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ በበኩላቸው ሰንደቅ አላማ ለሀገር ክብር መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖች አባቶችን የምናስታውስበት ነው ብለዋል።


 

ሰንደቅ አላማችን የመላው ብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት የአብሮነታችን እና የሕብረ ብሔራዊነታችን ማሳያ ነው ያሉት ደግሞ የአሪ ዞን የሽግግር ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ስመኝ ተስፋዬ ናቸው።


 

በክብረ በዓሉ ላይ ትርኢቶችና ኪነ-ጥበባዊ ስራዎች የቀረቡ ሲሆን በብሔራዊ መዝሙር ሰንደቅ አላማ የመስቀል ስነ-ስርዓት ተካሄዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም