ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የማንሰራራት ጅማሮዋን ባበሰረችበት ማግስት የሚከበረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን የተለየ ትርጉም አለው-ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)    

ወራቤ ፤ ጥቅምት 3/2018(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ የማንሰራራት ጅማሮዋን ባበሰረችበት ማግስት የሚከበረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን የተለየ ትርጉም አለው ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

 18ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን "ሰንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብስራት፣ ለብሄራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ህዳሴ"  በሚል መሪ ሀሳብ በወራቤ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡


 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ የማንሰራራት ጅማሬዋን ባበሰረችበት ማግስት የሚከበረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን የተለየ ትርጉም አለው፡፡

ኢትዮጵያ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በማጠናቀቅ ሌሎች ታላላቅ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እውን በማድረግ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የስኬት ጉዞዋን መጀመሯን ተናግረዋል፡፡


 

በኢትዮጵያ የተጀመሩ የለውጥ እሳቤዎችን ከዳር ለማድረስ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው (ዶ/ር) በስነ-ስርዓቱ ለይ ባስተላለፉት መልዕክት ጠቁመዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አንስተው በዚህም ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል፡፡


 

በክልሉ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት ለማጠናከር አብሮነትን የሚሸረሽሩ አስተሳሰቦችን ማስወገድ እንደሚገባ ጠቅሰው ለሁለንተናዊ ተጠቃሚነት መትጋት እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው (ዶ/ር) እና የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ስርሞሎ በጋራ በመሆን ሰንደቅ ዓላማ የመስቀል ስነ-ስርዓት ያከናወኑ ሲሆን ቃለ መሀላ የመግባት መርሃ ግብርም ተካሄዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የፌዴራል፣  የክልሉ፣ የዞን፣ የልዩ ወረዳና የወረዳ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም