በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተጀመሩ ቅንጅታዊ ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተጀመሩ ቅንጅታዊ ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል

ወራቤ ፤ጥቅምት 3/2018(ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተጀመሩ ቅንጅታዊ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለፀ፡፡
ቢሮው "የትምህርት ጥራት ለሁለንተናዊ ብልፅግና" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው 2ኛው የትምህርት ጉባኤ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በተገኙበት በወራቤ ከተማ እያካሄደ ነው፡፡
የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ፣ የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት የስራ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ እንዳሉት፡በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተጀመሩ ቅንጅታዊ ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
በዚህም በ2017 የትምህርት ዘመን በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ማህበረሰቡን በማሳተፍ 78 አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን የማሰራትና 691 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን የመገንባት ስራ ተሰርቶ ለአገልግሎት መብቃታቸውን ተናግረዋል፡፡
የተማሪዎችን መጠነ ማቋረጥ ለመቀነስም ከ118 ሺህ በላይ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
በዚህም የተማሪዎች ውጤት እየተሻሻለ መምጣቱን አንስተው ተግባሩን ለማጠናከር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡
የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ በበኩላቸው፤በዞኑ ለትምህርት ዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት ውጤታማ ለማድረግ ማህበረሰቡን ያሳተፈ ተግባር በመከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
በ2017 የትምህርት ዘመን የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻልና ለመፃህፍት ህትመት የሚሆን ከ376 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ በማሰባሰብ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
እንዲሁም በአዲሱ ፍኖተ ካርታ የተዘጋጀውን የተማሪዎች መፃህፍት በማሳተም ለተማሪዎች ማሰራጨት መቻሉን ጠቅሰው በዚህም ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡
በጉባኤውም በክልሉ በትምህርት ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት እንደሚደረግም ተመላክቷል፡፡