የሠንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ የተነደፉ ኢኒሼቲቮችን ከዳር ለማድረስ ቃል በመግባት ሊሆን ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሠንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ የተነደፉ ኢኒሼቲቮችን ከዳር ለማድረስ ቃል በመግባት ሊሆን ይገባል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2018 (ኢዜአ)፡- የሠንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ የተነደፉ ኢኒሼቲቮችን ከዳር ለማድረስ ቃል በመግባት ሊሆን እንደሚገባ የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት የሐብት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ብርሃኑ ፈይሳ ገለጹ።
18ኛው ብሄራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት አመራር እና ሰራተኞች በተገኙበት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት የሐብት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ብርሃኑ ፈይሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የቀደሙ አባቶች በከፈሉት የህይወት መስዋዕትነት የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ክብር ከፍ እንዲል አድርገዋል።
ቀደም ሲል የነበሩትም አሁን ያሉትም አትሌቶችም የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ በኩራት እንዲውለበለብ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን አንስተዋል።
ይሄ ትውልድ የአባቶች አደራ አለበት ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ የተነደፉ ኢኒሼቲቮች ላይ በመሳተፍ አደራውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አንድነትን በማጎልበት የተጀመሩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ከግብ ለማድረስ በጋራ መስራትን ማጠናከር እንደሚገባም ጠቁመዋል።
18ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን "ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ" በሚል መሪ ሃሳብ በመላ ሀገሪቱ በተለያዩ ኹነቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡