ቀጥታ፡

የዘንድሮው የሠንደቅ ዓላማ ቀን በዓል የሚከበረው ኢትዮጵያ በማንሰራራት ዘመን ላይ ባለችበት ወቅት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል-አብዱ ሁሴን (ዶ/ር )

ባሕርዳር፤ ጥቅምት 3/2018(ኢዜአ)፡- የዘንድሮው የሠንደቅ ዓላማ ቀን በዓል የሚከበረው  ኢትዮጵያ በማንሰራራት ዘመን ላይ ባለችበት ወቅት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ሲሉ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር ) ገለጹ። 

"ሠንደቅ  ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት  ፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ" በሚል መሪ ሀሳብ ለ18ኛ ጊዜ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዛሬ  በባሕር ዳር ከተማ ተከብሯል።


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ፣የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ ፣ የፌዴራልና የክልሉ   የፀጥታ አባላት እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና የተቋማት ሰራተኞች በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።

በዚህ ወቅት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ባደረጉት ንግግር፤  ሠንደቅ ዓላማ የሀገር ሉአላዊነትና ክብርና  የሀገር ርዕይ የሚገለፅበት ምልክት ነው ብለዋል።

የዘንድሮው የሠንደቅ ዓላማ ቀን በዓል የሚከበረው በእርግጥም ኢትዮጵያ በማንሰራራት ዘመን ላይ  ባለችበት ወቅት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

በተለይም የኢትዮጵያውያን የአብሮነት መገለጫ የሆነው ታላቁ ህዳሴ ግደብ የተጠናቀቀበትና ሌሎች አዳዲስ ፕሮጀክቶች የተጀመሩበት የማንሰራራት ዘመን ማሳያዎች ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።


 

በመሆኑም በሀገሪቱ የተጀመሩ ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች  ግንባታ ይበልጥ  ተጠናክሮ እንዲቀጥል በሠንደቅ ዓላማው ዙሪያ በመሰባሰብ ሀገርን መጠበቅ  ይገባናል ብለዋል።

የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ በበኩላቸው እንደገለጹት፤  የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ የጀግንነትና አይበሬነት ምልክት ነው።


 

የሠንደቅ አላማ ቀን ሲከበርም ጀግኖች አያቶች  አስከብረው ያቆዩትን ሀገራዊ ክብር ለመጪው ትውልድ ለማሸጋገር ጭምር ታስቦ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሠንደቅ አላማ የአልሸነፍም ባይነት እና የነፃነት ምሳሌ መሆኑን አንስተው ፤ የሠንደቅ ዓላማን  ክብር በመጠበቅ  ሁሉም በየተሰማራበት ለተሻለ ለውጥና እድገት  ተግቶ መስራት እንዳለበት  አመልክተዋል።

በዓሉ ብሔራዊ መዝሙር በመዘመር፣ ሠንደቅ ዓላማ በመስቀል እና የልማት ስራዎች ላይ ለመትጋት ቃለ መሃላ በመፈፀም ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም