ሠንደቅ ዓላማ በእያንዳንዱ ሠራዊት ልብ የታተመ የነፃነት መገለጫ ታላቅ የብሔራዊ ኩራት አርማ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሠንደቅ ዓላማ በእያንዳንዱ ሠራዊት ልብ የታተመ የነፃነት መገለጫ ታላቅ የብሔራዊ ኩራት አርማ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ በእያንዳንዱ ሠራዊት ልብ የታተመ የነፃነት መገለጫ ታላቅ የብሔራዊ ኩራት አርማ ነው ሲሉ የመከላከያ ሠራዊት የመረጃ ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና ገለፁ።
18 ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን "ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ" በሚል መሪ ሃሳብ በመላ ሀገሪቱ በተለያዩ ኹነቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡
በዚህም መሠረት በዓሉ በሀገር መከላከያ ጠቅላይ መምሪያ ተከብሯል።
በበዓሉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የመረጃ ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ጌታቸው ጉዲናን ጨምሮ የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ከፍተኛ ጄኔራል መኮንኖች እና በርካታ የሠራዊት አባላት ተገኝተዋል።
ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሠንደቅ ዓላማችን የሉዓላዊነታችን ነፀብራቅ፣ የነፃነት እና የአርበኝነት አሻራና መገለጫችን ነው ብለዋል።
ሠንደቅ ዓላማችንና የመከላከያ ሠራዊታችን ከቃል እስከ ህይወት መስዋዕትነት የተገመደ ቁርኝትና ትሥሥር አላቸው ብለዋል።
እያንዳንዱ የሠራዊት አባል በቀኝ ክንዱ፣ በመለዮውና፣ በየክፍሉ ባለው ዓርማ፣ በመስሪያ ቦታና ካምፑ ብሎም መስዋዕትነት ሲያጋጥመው ደግሞ መሸፈኛ እና ማጀቢያው ሠንደቅ ዓላማው ነው ብለዋል።
በዚህም ምክንያት ሠንደቅ ዓላማ ለሰራዊታችን የተለየ ትርጉም አለው ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ በእያንዳንዱ ሠራዊት ልብ የታተመ የሀገራዊ አንድነትና የነፃነት መገለጫ ታላቅ የብሔራዊ ኩራት አርማ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
በዚህም የሀገራችን እና የሰንደቋን ከፍታ ለማረጋገጥ በሚደረግ ጥረት ውስጥ እኛ የሠራዊት አባላትና አመራሮቹ እንደ ከዚህ ቀደሙ የተጣለብንን ሃላፊነት በትጋት ለመወጣት ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።