ቀጥታ፡

መንግስት ባህላዊ እሴቶች ለምተው ለቱሪስት መስህብና ለሁለንተናዊ ብልፅግና መሰረት እንዲሆኑ አድርጓል

አዲስ አበባ፣ጥቅምት 2/2018 (ኢዜአ)፡-መንግስት ተደብቀው የቆዩ ባህላዊ እሴቶች ለምተው ለቱሪስት መስህብና ለሁለንተናዊ ብልፅግና መሰረት እንዲሆኑ ማድረጉን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እፀገነት መንግስቱ ገለጹ።

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የአዳብና ፌስቲቫል መዝጊያ መርሃግብር ተካሂዷል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣የአካባቢው ተወላጆችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እፀገነት መንግስቱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፤ኢትዮጵያ አኩሪ የሆነ ብዝሃ ባህል ያላት አገር ናት።

ከለውጡ በኃላ አቧራ ለብሰው ተሸፍነው የቆዩ ባህሎች እያደጉ የቱሪስት መስህብ እየሆኑ በመምጣት የአገሪቱ ምድረ ቀደምትነት እየተገለፀ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ባህላዊ እሴቶች ለሁለንተናዊ ብልፅግና አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ማስቻሉን ገልጸዋል።

አዳብና ከጊዜ ወደጊዜ እየተረሳ መምጣቱን ጠቁመው፥ መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሳይበረዝ ወደቀድሞ ለመመለስ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዛሬ የተከበረው የአዳብና በዓል ማህበራዊ መስተጋብርንና በህዝቦች መካከል ያለ ትስስርን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

በበዓሉ ለሰላም እሴት ግንባታና በሁሉም ዘርፍ አስተዋፅኦ ያለው በመሆኑ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲቆይ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲ በበኩላቸው፥ አዳብና ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ማህበረሰብ ግንባታ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

ሚኒስቴሩ ባህላዊ ስርዓቶች በሚገባ ተጠንተውና ለምተው የአገር ብልፅግና ለማረጋገጥ እንዲውሉ ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ምክር ቤት አፈጉባኤ እንዳልካቸው ጌታቸው፥ አዳብና የሶዶ ክስታኔ ዋነኛ መገለጫ ከሆኑት ባህልና እሴቶች መካከል አንዱ መሆኑን ገልፀዋል።

አዳብና ከመስከረም 16 እስከ ጥቅምት 5 ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች በገበያና ሃይማኖት ቦታዎች የሚካሄድ ነው ያሉት ደግሞ በዞኑ የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ብሩክታዊት ፀጋዬ ናቸው።

የአክራሜ በጎ አድራጎት ሴቶች ማህበር ሰብሳቢ ሳራ ስዩም በበኩላቸው፥ የአዳብና በዓል የወጣቶች የነፃነትና የመተጫጨት በዓል መሆኑን ተናግረዋል።

በዓሉን በሀገርና በዓለም ደረጃ ለማስተዋወቅ ብሎም በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም