ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት ግንባታ ወሳኝ ሚና አለው - ኢዜአ አማርኛ
ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት ግንባታ ወሳኝ ሚና አለው

ወልቂጤ፤ጥቅምት 2/2018 (ኢዜአ) ፡-ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሕብረ ብሔራዊ አንድነት የሰፈነባት ጠንካራ ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ወሳኝ ሚና እንዳለው የሰላም ሚኒስቴር ገለፀ።
የሰላም ሚኒስቴር ለ14ኛ ዙር ያዘጋጀው ብሔራዊ የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት ስልጠና በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ መሰጠት ተጀምሯል።
"በጎነት ለአብሮነት" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በተጀመረውና ለአንድ ወር በሚቆየው ስልጠና ከአንድ ሺህ በላይ ወጣቶች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ፍሬሰንበት ወልደተንሳይ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የወጣቶችን የሀገርና የሕዝብ ፍቅር ለማሳደግ አስተዋጾ እያደረገ ነው።
አገልግሎቱ በተለይ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት የሰፈነባት ጠንካራ ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ወሳኝ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።
ዛሬ ለወጣቶች መሰጠት የተጀመረው ስልጠናም ኢትዮጵያዊ እሴቶችንና መርሆችን ለወጣቱ ትውልድ ለማስረጽ ያለው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል።
ወጣቶቹ በቀጣይ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ የሥራ ባህልን በማጎልበት፣ በህይወት ክህሎት፣ መልካም ስነምግባርን በማስረጽና እና በሀገራዊ አንድነት ላይ እንደሚሰሩም አመልክተዋል።
በዚህም በህብረተሰቡ ውስጥ አስተሳሳሪ ገዥ ትርክትን በማስረፅ ለሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን መጠናከር፣ ለዘላቂ ሠላም ግንባታና ልማት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ተናግረዋል።
እንደእሳቸው ገለጻ ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወንድማማችነትና እህታማማችነትን ለማጎልበት፣ ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችን ለማወቅና ከአካባቢ ባሻገር ሀገራዊ አስተሳሰብን ለማዳበር ይረዳል፡፡
"ሁሉም ዜጋ ለሰላምና ልማት መረጋገጥ አምባሳደር መሆን አለበት" ያሉት ደግሞ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት የሺሀረግ አፈራ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
በስልጠናው ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ወጣቶች እየተሳተፉ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ወጣቶቹ ባህልና እሴቶቻቸውን ለሌሎች በማስተዋወቅ አብሮነትን ለማጠናከር የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው በሀገሪቱ ያሉና ለህዝቦች ትስስር ምሶሶ የሆኑ ዕሴቶች እንዲጎለብቱ በመሰነድና ለትውልድ እንዲሸጋገሩ በማድረግ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ላእመቾ ፍቅሬ እና ህይወት ኤልያስ ስልጠናው በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ እሴቶችን የበለጠ ለመረዳት ከሚሰጠው እድል ባለፈ በህይወት ክህሎት ላይ የተሻለ ዕውቀት የሚያስጨብጥ ነው ብለዋል፡፡
እንደሀገር የተጀመሩ ትልልቅ የልማት ሥራዎችን ለማጠናከር በሰላም፣ በብሔራዊ መግባባትና በአብሮነት ላይ ለመስራት ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል፡፡