በሶማሌ ክልል የሚከናወኑ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ህዝቡ በጉልበቱና በገንዘቡ ለመደገፍ ዝግጁ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል የሚከናወኑ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ህዝቡ በጉልበቱና በገንዘቡ ለመደገፍ ዝግጁ ነው

ጅግጅጋ፣ ጥቅምት 2/2018 (ኢዜአ)፡-በሶማሌ ክልል የሚገነቡ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ህዝቡ በጉልበቱና በገንዘቡ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ የተመረቁ ፕሮጀክቶችና የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠላቸው ፕሮጀክቶችን የሚደግፉ ሰልፎች በተለያዩ የክልሉ ከተሞች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ተካሂደዋል።
የድጋፍ ሰልፉ ደገሀቡር፣ ቀብሪደሀርና ጎዴ ከተሞችን ጨምሮ በሁሉም የዞንና የወረዳ መዋቅሮች ተካሂዷል።
የሰልፉን ዓላማ በማስመልከት ለኢዜአ ማብራሪያ የሰጡት የክልሉ መንግስት ኮሙንኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ መሀመድ አዳን፣ ከለውጡ በኋላ በክልሉ እየተካሄዱ ባሉ የልማት ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።
በዚህም የክልሉ ህዝብና መንግስት ተጠቃሚና ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ህዝቡ ለተከናወኑ የልማት ሥራዎችና በቀጣይ ለሚከናወኑ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ያለውን ድጋፍና ምስጋና ለመግለጽ በተለያዩ ከተሞችና መዋቅሮች ሰልፍ ማካሄዱን ተናግረዋል።
በድጋፍ ሰልፎቹ ህዝቡ ደስታውንና ድጋፉን ከመግለጽ ባለፈ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በክልሉ በቅርቡ ላስጀመሯቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች እንዲሁም የተፈጥሮ ጋዝ ሥራ ምስጋና ለማቅረብ ያለሙ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በተለይ በክልሉ የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ስራ መግባት የሀገርንም ሆነ የክልሉን ኢኮኖሚያዊ እድገት የማፋጠን ሚናው የጎላ መሆኑን የገለጹት አቶ መሀመድ፣ ህዝቡ የልማት ፕሮጀክቶቹ ፈጥነው እንዲጠናቀቁ የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጧል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የክልሉ ህዝብ ከልማት ተጠቃሚ እንዲሆን እየሰጡት ላለው የላቀ አመራርም ህዝቡ በሰልፉ ማመስገኑን ጠቅሰው፣ ፕሮጀክቶቹን በጉልበትና በገንዘብ በመደገፍ የራሱን ሃላፊነት ለመወጣት ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየቱንም አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ለተጀመሩ ሜጋ የልማት ፕሮጀክቶች ህዝቡ የሚያደርገውን ድጋፍና ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋገጡበት ሰልፍ መሆኑንም አንስተዋል።
እንደ አቶ መሀመድ ገለጻ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች የሕብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች እየመለሱ በመሆናቸው ህዝቡ ተጠቃሚ እየሆነ መጥቷል።