ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ- የጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ- የጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 2/2018(ኢዜአ)፦መንግሥት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የዓለም የልብ ቀን "አንድም የልብ ምት አታምልጠን" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በአዲስ አበባ በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።
በእለቱም የኢትዮጵያ የልብ ማህበር አባላት፣ የህክምና ባለሙያዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ቀኑን ምክንያት በማድረግ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና የእግር ጉዞ አካሒደዋል።
ጤና ሚኒስቴርን በመወከል የተገኙት አቶ ሌሊሳ አማኑኤል፤ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት በማሕበረሰቡ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ካሉ ችግሮች ዋነኛው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ናቸው።
በዚሁ ሳቢያም መንግስት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል የሚያስችል የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ የተጠናከሩ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ከዚህ ውስጥም የባለሙያዎች አቅም በማጠናከር፣ መድሃኒቶች ከውጭ በማስገባት እና የልብ ቀዶ ጥገናዎች በዘመቻ እንዲካሔዱ የማድረግ ተጠቃሽ ስራዎች ናቸው ብለዋል።
መንግስት በሽታውን ለመከላከል ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ዜጎች አመጋገባቸውን በማስተካከል እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ራሳቸውን የመጠበቅ ባሕል ሊያጎለብቱ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ የልብ ማኅበር ፕሬዝደንት እንዳለ ገብሬ በበኩላቸው፤ ማህበሩ የዓለም አቀፉ የልብ ቀን ምክንያት በማድረግ የልብ ህክምናዎችን ከመስጠት ባሻገር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ከልብ ህመም ጋር ተያይዞ ሕክምና ለማግኝት በርካታ ዜጎች ተራቸውን በመጠባበቅ ላይ በመሆናቸው ይህንኑ ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በአሁኑ ወቅትም ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን በተለይ በትምህርት ቤቶች የልብ ህመም ጋር ተያይዞ ህክምና የሚፈልጉ ዜጎችን መረጃ የመለየት ስራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ማሕበሩ የሕዝብ መድሃኒት ቤቶችን በመክፈት ለረዥም ጊዜ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት መድሃኒት ለሚወስዱ ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል።
የልብ ህመም በሕብረተሰቡ ላይ አያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመቀነስም በየወቅቱ ምርመራ የማድረግ ባሕልን ማጎልበት እንደሚገባም ነው የጠቀሱት።
በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙ ከልብ ህመም ጋር ተያይዞ ህክምና የወሰዱ ታካሚዎች በበኩላቸው፤ማሕበረሰቡ የልብ ህመም የሚያመጡ በሽታዎች ምልክቶችን ሲያይ ፈጥኖ ወደ ሕክምና በመሄድ ህክምና ማድረግ እንደሚገባ ይመክራሉ።
አስተያየት ሰጪዎቹ ወይዘሮ እመቤት አሰሙ እና ወይዘሮ ሚዛን ሀጎስ፤ ልብ ህክምና ከባድና ብዙ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ አገልግሎት አሰጣጡ ላይ በቅንጅት ቢሰራ አቅም የሌላቸው ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል ነው የሚሉት።