ቀጥታ፡

ኪነ-ጥበብን ለልማትና ለሀገራዊ ትርክት ግንባታ ማዋል ይገባል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 2/2018 (ኢዜአ)፦ኪነ-ጥበብን ለሀገራዊ ልማትና ትርክት ግንባታ ይበልጥ መጠቀም እንደሚገባ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በየወሩ የሚያዘጋጀው የስነ-ጽሁፍ ምሽት "ድህረ ህዳሴ" በሚል መሪ ሀሳብ ተዋቂ ግለሰቦች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተከናውኗል፡፡


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ስራ አስፈጻሚ ነጋሲ አምባዬ በወቅቱ፥ ኢትዮጵያ የቁጭት ዘመን አብቅቶ የማንሰራራት ዘመን ላይ እንደምትገኝ ተናግረዋል።

ይህንን አዲስ ምዕራፍ በሚገባ ለመግለጽና ለማሳየት የኪነጥበብ ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም ይህንኑ ለማሳደግ መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ኪነ-ጥበብ የሀገርን ልማት በማፋጠን ሂደት ውስጥ ትልቅና አዎንታዊ ሚና ለማሳደግም ሚዲያ ያለውን አበርክቶ እውን በማድረግ ልማትንና ገጽታ ግንባታን ለማፋጠን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን የተዘጋጀው የኪነ-ጥበብ ምሽትም የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ ያለመና የጋራ ትርክትን የሚፈጥሩ አጀንዳዎችን ለማንሸራሸር ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

በኪነ-ጥበብ ምሽቱ ላይ የተገኙት የዓባይ ንጉሶች ሚዲያ መስራች ኡስታዝ ጀማል በሽር በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያውያን በትብብር ታላቁን የሕዳሴ ግድብ በማጠናቀቅ ታሪክ መሥራታቸውን ገልጸዋል።

በዚህ ታሪካዊ ሂደት ውስጥ ኪነ-ጥበቡ ከፍተኛ ሚናውን እንደተጫወተ አንስተዋል።

የኪነ-ጥበብ አቅምን በማጎልበት በሕዳሴው ግድብ ያሳየነውን ህብረት በሌሎች የልማት ዘርፎች ላይም መድገም እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የስነ-ጥበብ ኮሌጅ ዲን አገኘሁ አዳነ፥ ኪነ-ጥበብ በሀገር ግንባታ ያለውን ትልቅ አበርክቶ በመጠቀም ህብረተሰብን ለልማት ማነሳሳት እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

የለውጡ መንግሥት የኪነ-ጥበብ ዘርፍን ለማሳደግ በሰጠው ትኩረት ክዋኔ ጥበባት መድረኮች እንዲስፋፉ ማድረጉን አንስተዋል።

ይህም የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ለሰብዓዊና ለሀገር ልማት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ እድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል።

በኪነጥበብ ምሽቱ መርሃ ግብር ላይ፣ ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ጋር ተያይዘው የተዘጋጁ ግጥሞች፣ መጣጥፎች እና ሌሎች የስነ-ጽሁፍ ስራዎች ቀርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም