የአዳብና የእርስ በርስ መስተጋብርን ለማጠናከርና ለሰላም እሴት ግንባታ አስተዋጽኦ ያለው በዓል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአዳብና የእርስ በርስ መስተጋብርን ለማጠናከርና ለሰላም እሴት ግንባታ አስተዋጽኦ ያለው በዓል ነው

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 2/2018(ኢዜአ)፦የአዳብና በዓል የእርስ በርስ መስተጋብርን ለማጠናከርና ለሰላም እሴት ግንባታ አስተዋጽኦ ያለው በዓል መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እፀገነት መንግስቱ ገለፁ።
የምስራቅ ጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የአዳብና ፌስቲቫል መዝጊያ መርሃግብር እየተካሄደ ይገኛል።
በመርሃግብሩ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ የአካባቢው ተወላጆችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በዚህ ወቅት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እፀገነት መንግስቱ እንዳሉት ኢትዮጵያ አኩሪ የሆነ ብዝሃ ባህል ያላት አገር ናት።
ከለውጡ በኃላ አቧራ ለብሰው ተሸፍነው የቆዩ ባህሎች እያደጉ መስህብ እየሆኑ በመምጣት የአገሪቱ ምድረ ቀደምትነት እየተገለፀ መሆኑን ተናግረዋል።
አዳብና ከጊዜ ወደጊዜ እየተረሳ መምጣቱንና መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሳይበረዝ ወደቀድሞ ለመመለስ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዓሉ ማህበራዊ መስተጋብርንና በህዝቦች መካከል ያለ ትስስርን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
በበዓሉ ለሰላም እሴት ግንባታና በሁሉም ዘርፍ አስተዋፅኦ ያለው በመሆኑ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲቆይ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲ በበኩላቸው፤ አዳብና ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ማህበረሰብ ግንባታ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
ሚኒስቴሩ ባህላዊ ስርዓቶች በሚገባ ተጠንተውና ለምተው የአገር ብልፅግና ለማረጋገጥ እንዲውሉ ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።
የምስራቅ ጉራጌ ዞን ምክር ቤት አፈጉባኤ እንዳልካቸው ጌታቸው አዳብና የሶዶ ክስታኔ ዋነኛ መገለጫ ከሆኑት ባህልና እሴቶች መካከል አንዱ መሆኑን ገልፀዋል።
አዳብና የመተጫጫ፣ የነፃነት እንዲሁም የተጠፋፉ ወዳጆች የሚገናኙበት የወጣቶች እና የልጃገረዶች በዓል ዝግጅት ከመስከረም 16 እስከ ጥቅምት 5 ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች በገበያና ሃይማኖት ቦታዎች የሚካሄድ መሆኑን ተናግረዋል።
በዓሉን በሀገርና በዓለም ደረጃ ለማስተዋወቅ ብሎም በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሰራ ነው ብለዋል።