ቀጥታ፡

ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ሀገራዊ አንድነት ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የወጣቶች ተሳትፎ ወሳኝ ነው-የሰላም ሚኒስቴር

ደሴ፤ጥቅምት 2/2018 (ኢዜአ)፦ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ሀገራዊ አንድነት ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የወጣቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ 14ኛ ዙር ብሔራዊ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች ስልጠና በወሎ የኒቨርሲቲ አስጀምሯል።

በሰላም ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ አቶ አበበ ወርቁ በስልጠናው እንደገለጹት፥ ዘላቂ ሰላምና ልማትን በማረጋገጥ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን እውን ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ ነው።

ለዚህም ሚኒስቴሩ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ላሉ ወጣቶች በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስልጠና በመስጠት ሀገራዊ መግባባትን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ወጣቶች የኢትዮጵያውያንን የአብሮነት እሴት በማጎልበት ለሕብረተሰቡ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጡበትንና የእርስ በእርስ ግንኙነትን የሚያጠናክሩበትን አቅም ለመፍጠር እየሰራ መሆኑንም አቶ አበበ ተናግረዋል።

ወሎ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በአምስት ዩኒቨርሲቲዎች ስልጠናው እየተሰጠ መሆኑንና ለአንድ ወር እንደሚቆይ ገልጸው፥ በስልጠናው ከ6 ሺህ በላይ ወጣቶች ይሳተፋሉ ብለዋል።

እንደ አማካሪው ገለጻ ስልጠናው በሀገር ፍቅር፣በሰብዕና ግንባታ፣ በስነ ምግባር፣ በብሔራዊ መግባባትና በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ወጣቶች ተጨማሪ እውቀት እንዲጨብጡ የሚያደርግ ነው።

ባለፉት ለ13 ዙር በተሰጡ ስልጠናዎች ከ100 ሺህ በላይ በጎ ፍቃድ ወጣቶች ስልጠና ወስደው ሕብረተሰቡን በበጎ ፍቃድ ከማገልገል ባለፈ ለተለያየ ኃላፊነት የበቁበት ሁኔታ እንዳለም አመልክተዋል።

የወሎ የኒቨርሲቲ አስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ አቶ ጌትነት ካሴ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲተው ሰላምን ለማጠናከርና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት በጥናትና ምርምር የበኩሉን እገዛ እያደረገ ነው።

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ሳይመን ኮች በሰጠው አስተያየት፣ በየአካባቢው ያሉ የተለያዩ ባህሎች፣ ቋንቋና የተፈጥሮ ሀብቶችን አውቆ ሀገራዊ አንድነት ለመፍጠር በሚሰሩ ሥራዎች የድርሻውን ለመወጣት መዘጋጀቱን ገልጿል።

የወጣቶችን ማህበራዊ ተሳትፎ ለማሳደግ በሚሰጠው ስልጠና ላይ መሳተፉ ይህን እውን ለማድረግ እንደሚያግዘውም ተናግረዋል።

ስልጠናው ህብረ ብሔራዊነትንና አንድነትን በማጠናከር ለሀገር እድገት በጋራ እንድንሰራ መሰረት ይጥላል ያለችው ደግሞ ወጣት ረምላ መሀመድ ናት።

በስልጠናው የምናገኘው እውቀት ሕብረተሰቡን በበጎ ፈቃድ እንድናገለግልና ሰላማችንን እንድናጸና ተጨማሪ አቅም ይሆናል ብላለች።

በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም