አገልግሎቱ ከነበረብን ችግር ወጥተን አዲስ ሕይወት እንድንጀምር ተስፋ ሰጥቶናል - ኢዜአ አማርኛ
አገልግሎቱ ከነበረብን ችግር ወጥተን አዲስ ሕይወት እንድንጀምር ተስፋ ሰጥቶናል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 2/2018 (ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት ያገኙት ድጋፍ ከነበረባቸው ሱስ ተላቀው አዲስ የሕይወት ምዕራፍ እንዲጀምሩ ተስፋ እንደሆናቸው ቀደም ሲል በተለያየ ሱስ ተጠምደው የነበሩ ግለሰቦች ገለጹ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው በተለያየ ሱስ ተጠምደው የነበሩ ግለሰቦች የቤተሰብ መበታተን፣ የሥራ ማጣት እና የከፍተኛ የጤና መቃወስ አደጋ እንዳስከተለባቸው ይናገራሉ።
ነገር ግን፣ በኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት ያገኙት ድጋፍ ለብዙዎች ከጨለማው ጉዞ ወጥተው አዲስ የሕይወት ምዕራፍ እንዲጀምሩ እንዳስቻላቸው ይገልፃሉ፡፡
ወጣት እንዳለልኝ ታዬ ለዓመታት በመጠጥና በጫት ሱስ ሲሰቃይ እንደነበር ይናገራል።
ሱሱ በሕይወቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰበትና ወደ ውድቀት እንዳመራው በቁጭት ይገልጻል፡፡
ከዚህ አስከፊ ሕይወት ለመውጣት መወሰኑን ተከትሎ ወደ አገልግሎቱ መግባቱን ከሱስ ነጻ መሆን መቻሉን በደስታ ይናገራል።
በተመሳሳይ፣ ጌትነት ተረፈ በአገልግሎቱ ውስጥ ባሳለፋቸው ጊዚያት ከሱስ ነጻ የሚያደርገውን አገልግሎት እና እንክብካቤ ማግኘቱን ይገልጻል፡።
ጌትነት የሥነ ልቦና ድጋፍን ጨምሮ የተለያዩ አስፈላጊ አገልግሎቶች እንደተሰጠው ጠቅሶ፣ በተደረገለት በቂ ድጋፍና እንክብካቤ ምክንያት ከሱስ ነጻ መሆኑን አመላክቷል።
አዲስ ሕይወት የጀመሩት እነዚህ ተጠቃሚዎች ለቀጣይ ሕይወታቸውን ለመቀየር ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት፣ በትጋት ሠርተው ሕይወታቸውን ለመለወጥ እንደሚሠሩ ተናግረው፤ ወጣቶች ራሳቸውን ከሱስ እንዲጠብቁ አጥብቀው መክረዋል።
የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ገረመው ወንዶ በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ በተለያዩ ሱሶች የተጠመዱ ግለሰቦች ከነበረባቸው ችግር እንዲላቀቁ በትጋት እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ወደ አገልግሎቱ ለሚመጡ ግለሰቦች ከሱስ እንዲያገግሙ ከሚረዳ ድጋፍ በተጨማሪ፣ ወደ ሥራ እንዲመለሱ የሚያስችላቸውን የክህሎት ሥልጠና ጭምር እንደሚሰጥ አብራርተዋል።
በቀጣይ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሳደግ የማስፋፊያ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ በሱስ ችግር የተጠቁ ወደ ማዕከሉ በመምጣት አገልግሎት እንዲያገኙ ጥሪ አቅርበዋል።