ቀጥታ፡

የምርት ብክነትን ለመቀነስና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የግብርና ሜካናይዜሽን በስፋት ጥቅም ላይ የማዋሉ ተግባር ይጠናከራል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 2/2018 (ኢዜአ)፡-የድህረ ምርት ብክነትን ለመቀነስና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አርሶ አደሩ የግብርና ሜካናይዜሽንን በስፋት ጥቅም ላይ እንዲያውል የሚደረጉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የምርት ብክነትን በመቀነስ የዜጎችን የምግብ ዋስትና እና ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው። 

ከዚህ ውስጥም አርሶ አደሩ ሜካናይዜሽን የሆኑ የመውቂያ፣ የማጨጃና የምርት መሰብሰቢያ መሳሪያዎችን እንዲጠቀም በማድረግ የምርት ብክነትን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑም ተጠቁሟል።

በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ኢሳያስ ለማ ለኢዜአ እንዳሉት ግብርናውን በማዘመን የምርት ብክነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው።

በተለይም ሰብል በሚዘራበት፣ በሚወቃበትና በሚሰበሰብበት ወቅት ሜካናይዜሽን የእርሻ መሳሪያዎችን በማሰራጨትና አርሶ አደሩ ጥቅም ላይ እንዲያውላቸው  እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በአሁኑ ወቀት በተለይም የበልግ ምርት የሚሰበሰብበት ወቅት በመሆኑ ብክነትን ለመቀነስ የተጠናከሩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዋናነትም ስንዴ በሚያመርቱ አካባቢዎች የመውቂያ ኮምባይነር በስፋት እየተሰራጨ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ምርታና ምርታማነትን ለማሳደግ አርሶ አደሩ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም እየተደረገ ነው።

በተለይም በኩታ ገጠም የሚያርሱ አርሶ አደሮችን በማደራጀት በጋራ እንዲሰሩና የምርት ብክነትን እንዲከላከሉ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የምርት ብክነት ከዘር ወቅት አንስቶ ምርቱ ወደ ጎተራ እስኪገባ የሚከሰት በመሆኑ አርሶ አደሩ ዘመናዊ እርሻ መሳሪያዎችን እንዲጠቀም እየተደረገ ነው ብለዋል።

በተለይ አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ ብክነት የሚደርሰው በሚጓጓዝበት ወቅት በመሆኑ በዋናነት ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች የተሻሉ ማጓጓዛዎች እንዲጠቀሙ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ብክነትን መቀነስ ምርትና ምርታማነትን መጨመር ነው የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ብክነትን ለመቀነስ የሚከናወኑ ተግባራት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ በአገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያበረክታል ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም