ፋብሪካው በሀገር ውስጥ መገንባቱ በሚፈለገው ጊዜ፣መጠን እና ዓይነት ማዳበሪያ ለማግኘት ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
ፋብሪካው በሀገር ውስጥ መገንባቱ በሚፈለገው ጊዜ፣መጠን እና ዓይነት ማዳበሪያ ለማግኘት ያስችላል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 2/2018 (ኢዜአ)፡-ፋብሪካው በሀገር ውስጥ መገንባቱ በሚፈለገው ጊዜ፣መጠን እና ዓይነት ማዳበሪያ ለማግኘት እንደሚያስችል ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት እና ፍላጎትን በራስ ዐቅም ለመሸፈን የሚደረገው ጥረት ያጋጥሙ የነበሩ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን እንደሚቀርፍም አመልክቷል።
የማዳበሪያ ፋብሪካው በሀገር ውስጥ መገንባቱ ያለውን ፋይዳ በሦስት ዋና ዋና ዘርፎች ጠቅልሎ መግለጽ እንደሚቻል በሚኒስቴሩ የግብዓት አቅርቦት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንግሥቱ ተስፋ ለኢዜአ ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት የመጀመሪያው ጥቅሙ ማዳበሪያ በምንፈልግበት ጊዜ፣ መጠን እና ዓይነት እንድናገኝ የሚያስችል መሆኑ ነው ብለዋል።
የአቅርቦት ሰንሰለትን እና ጊዜን የሚያሳጥር መሆኑ ደግሞ ሁለተኛው የፋብሪካው በሀገር ውስጥ መገንባት ፋይዳ መሆኑን አንስተዋል።
ከውጭ ሀገር ማዳበሪያ ሲገዛ ከጨረታ እስከ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ድረስ ባለው ሂደት የተንዛዛ ሰንሰለትን ማለፍ እና ረዥም ጊዜ መፍጀት አስገዳጅ መሆኑን አስረድተዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች የአፈር ማዳበሪ ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ እየናረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሦስተኛው የፋብሪካው ጥቅም ወጪ መቀነስ መሆኑን አስገንዝበዋል።
መንግሥት በከፍተኛ ድጎማ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚያስገባ ጠቅሰው፤ በ2017 ዓ.ም ብቻ 84 ቢሊየን ብር ድጎማ ማድረጉን አረጋግጠዋል።
በሀገር ውስጥ ማምረት ሲጀመር ለመርከብ ማጓጓዣና ለወደብ ኪራይ ይወጣ የነበረን ወጪ ያስቀራል ብለዋል።
አስተማማኝ አቅርቦትና ሀገራዊ የማድረግ ዐቅምን የሚያሳድግ መሆኑን ያስረዱት አቶ መንግሥቱ፤ ለአርሶ አደሩም ማዳበሪያውን በወቅቱ ለማቅረብ እንደሚያስችል ነው ያስገነዘቡት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መስከረም 22 ቀን 2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመተባበር የሚገነባውን የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጣቸው ይታወሳል።