ቀጥታ፡

የወጣቱን የበጎ ፍቃድ አገልግሎትና የሰላም አምባሳደርነት ሚና የሚያሳደጉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ--የሰላም ሚኒስቴር

ጅማ፣ ጥቅምት 2/2018(ኢዜአ)፡-የወጣቱን የበጎ ፍቃድ አገልግሎትና የሰላም አምባሳደርነት ሚና የሚያሳደጉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሰላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት የሚተገበረው የ14ኛ ዙር የወጣቶች "የበጎነት ለአብሮነት" ስልጠና ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።


 

በስልጠናውም በቀጣይ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ብሔራዊ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጡ 1ሺህ ወጣቶች እንድሚሳተፉም ተመላክቷል።

በሰላም ሚኒስቴር የብሔራዊ በጎ ፍቃድ ማህበረሰብ ልማት አገልግሎት ፕሮግራም መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገመቺሳ ኢቲቻ በመርሀ ግብሩ ላይ እንዳሉት ወጣቱ በማህበራዊ በጎ ፍቃድ አገልግሎት መሪ እንዲሆን  እየተሰራ ነው ።

በተለይ ማህብረሰቡን በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በማገዝ ማህበራዊ ሀላፊነቱን እንዲወጣ የማስተባበር ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ገመቺስ ገለጻ ወጣቶች ለዘላቂ ሰላምና የህዝቦች አብሮነት ይበልጥ ተግተው እንዲሰሩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

ለተግባራዊነቱም ሰላም ሚኒስቴር ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ወጣቶችን በ13 ዙር በማሰልጠን በተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው ብሔራዊ በጎ ፍቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን አስታውሰዋል።

ይህም ሰላምን ከማጠናከር፣ በህዝቦች መካከል አብሮነትን ከማጎልበትና ብሔራዊ መግባባትን ከመገንባት አንጻር ጉልህ ሚና  እንዳለው ነው የገለጹት።

የወጣቱን የበጎ ፍቃድ አገልግሎትና የሰላም አምባሳደርነት ሚናን የሚያሳደጉ ተግባራት በቀጣይም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉም አቶ ገመቺስ ተናግረዋል።


 

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ኢንጂነር ኤፍሬም ዋቅጅራ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በተለያዩ ዙሮች ለህብረተሰቡ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶችን ተቀብሎ ማሰልጠኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም ዩኒቨርሲቲው ከ1 ሺህ በላይ ወጣቶችን ተቀብሎ እንደሚያሰለጥን ገልጸው ዛሬ የተጀመረው ስልጠና ለአንድ ወር እንደሚቆይ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም