ሠንደቅ ዓላማ የማንነታችን መለያ የእኛነታችን ጌጥ ነው - የመከላከያ ሰራዊት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ሠንደቅ ዓላማ የማንነታችን መለያ የእኛነታችን ጌጥ ነው - የመከላከያ ሰራዊት አባላት

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 2/2018(ኢዜአ)፦ሠንደቅ ዓላማ ከአባቶቻችን የወረስነው የማንነታችን መለያ የእኛነታችን ጌጥ ነው ሲሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ገለጹ።
18 ኛው የብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማ ቀን ነገ ሰኞ ጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ይከበራል።
ሠንደቅ ዓላማ የብሔራዊ አንድነት መገለጫ፤ የአንድ አገር ዜጎች አገራዊ ፍቅርና ብሔራዊ ስሜትን የሚገልፁበት፤ ታሪካዊ ትስስርና ስነ-ልቦናዊ አንድነት የሚንፀባረቁበት የአገራዊ አንድነትና ህብረት አርማ ነው።
በመሆኑም ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ በመጀመሪያው ሳምንት ሰኞ እንዲከበር በህግ ተደንግጓል።
በዓሉ በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች እና በሌሎች ዓለማት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ሠንደቅ ዓላማ በመስቀል እና በሰንደቅ ዓላማ ፊት ቃለ መሐላ በመፈፀም በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።
በዓሉን አስመልክተው ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ሚኒሊክ ዋለ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የምትታወቀው የምትወከለው በሠንደቅ ዓላማዋ ነው።
ሠንደቅ ዓላማ ይበልጥ የሚገለጸውም በመከላከያ ሰራዊቱ መሆኑን ገልጸው፤ በተልእኮዎቹ ሁሉ የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ ይዞ እንደሚንቀሳቀስ ጠቁመዋል።
በዚህም የበዓሉ መከበር ለሰራዊቱ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ በኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ አካዳሚክ ዲን ኮሎኔል መሰረት ሞላ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ረጅም ታሪክ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
ሠንደቅ ዓላማ አርማ ብቻ ሳይሆን ከአባቶቻችን የወረስነው የማንነታችን መገለጫ ነው ብለዋል።
ኮሎኔል ሚኒሊክ ዋለ (ዶ/ር) ሠንደቅ ዓላማ አባቶቻችን እና እናቶቻችን መስዋእትነት ከፍለው ከዘመን ዘመን አሻግረው የሰጡን የማንነት መለያ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሰራዊቱ ለሠንደቅ ዓላማ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸው፤ በዓሉ በየቀኑ መከበር ያለበት መሆኑን አመላክተዋል።
ኮሎኔል መሰረት ሞላ (ዶ/ር) ሠንደቅ ዓላማ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ልዩ ትርጉም ያለው መሆኑን አንስተዋል።
ሀገርን የመጠበቅ ሀላፊነት ለተጣለበት የመከላከያ ሰራዊት የበዓሉ መከበር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አመላክተዋል።