ቀጥታ፡

የጀግንነት ምልክትና የህብረ ብሔራዊ አንድነት መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ክብር ጠብቆ መዝለቅ የትውልዱ አደራ ሊሆን ይገባል-የቀድሞ ሠራዊት አባላት

ወላይታ ሶዶ፤ጥቅምት 2/2018 (ኢዜአ)፦የጀግንነት ምልክትና የህብረ ብሔራዊ አንድነት መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ክብር ጠብቆ መዝለቅ የትውልዱ አደራ ሊሆን ይገባል ሲሉ የቀድሞ ሠራዊት አባላት ተናገሩ።

የቀድሞ መከላከያ ሠራዊት አባል ሻምበል አንጁሎ ኦልባሞ እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷ ከነሙሉ ክብሯ ተጠብቆ ታፍራና ተከብራ የቆየውችው በየዘመናቱ ልጆቿ በከፈሉት መስዋዕትነት ነው።

የአሁኑ ትልድ በጀግኖች ልጆቿ የአጥንትና ደም መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል ጸንታ ለቆየችው ኢትዮጵያና ለሰንደቅ ዓላማ ተገቢውን ክብር እንዲሰጥ የባንድራን ምንነት ማስረጽ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ክብሩ ከሀገርም የተሻገረ የጥቁር ህዝቦች ሁሉ የነፃነት ምልክት መሆኑን ገልጸው፣ በዚሁ ልክ ሁሉም ክብር መስጠት እንዳለበት አመልክተዋል።

ሌላው የቀድሞ መከላከያ ሠራዊት አባል የነበሩትና በክብር የተሰናበቱት ሻለቃ ጳውሎስ ገብረስላሴ በበኩላቸው፥ ለኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ክብር ሲሉ በየዘመናቱ በርካታ ጀግኖች ዋጋ እየከፈሉ ሀገርን እስከዛሬ አስቀጥለዋል።

የሰንደቁ ክብርና የሀገር ሉአላዊነት አሁንም በጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት መጠበቁ ሁሉንም የሚያስደስት ተግባር ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በመሆኑም የጀግንነት ምልክትና የህብረ ብሔራዊ አንድነት መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ክብር ጠብቆ መዝለቅ የትውልዱ አደራ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በነገው እለት በብሔራዊ ደረጃ "ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ለብሔራዊ አንድነታችን፣ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮያ ሕዳሴ!” በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም