በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመሳተፍ የማህበረሰቡን ችግር ለማቃለል እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመሳተፍ የማህበረሰቡን ችግር ለማቃለል እየተሰራ ነው

አዳማ፤ጥቅምት 2/2018(.ኢዜአ)፦በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በንቃት በመተሳተፍ የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ማቃለል ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ ገለፁ።
በኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽን አዳማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በአዳማ ከተማ ዳቤ ክፍለ ከተማ የተገነባው የከለቾ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዛሬ ተመርቋል።
በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ፣ የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ፣ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ የስራ ሃላፊዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ በወቅቱ እንደገለፁት፥ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በንቃት በመተሳተፍ የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ማቃለል ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው።
"በአዳማ ከተማ በትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን የአቅመ ደካማ ቤቶችን ገንብተን አስረክበናል" ብለዋል።
የትምህርት ቤቱ ግንባታ ዘመናዊ የመማሪያ ክፍሎችና የመምህራንና አስተዳደር ቢሮዎችን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቱ በዕውቀትና ክህሎት የዳበረ ትውልድ ለመገንባት አስተዋጾው የጎላ መሆኑን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው፥ ኮሚሽኑ የሀገር ልማትና ዕድገት ለማስቀጠል የሚያግዘውን ገቢ ከማስገባት ባለፈ በበጎ ተግባር በስፋት እየተሳተፈ ይገኛል ብለዋል።
የትምህርት መሰረተ ልማትን ጨምሮ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ አስፈላጊውን ገቢ ከመሰብሰብ አኳያ የጀመርነውን ተግባር አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም አክለዋል።
ኮሚሽኑ ከመደበኛ ስራው በተጓዳኝ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመሳተፍ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች እንዲሁም የትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ላጋጠማቸው ተማሪዎች በአይነትና በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል።
በአዳማ ከተማ ሶሎቄ ዶንጎሬ ወረዳ የተገነባው የከለቾ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም የዚሁ አካል መሆኑን አስታውቀዋል።
የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ብልቶሳ ሂርኮ (ዶ/ር) እንደገለፁት፥ የክልሉ መንግስት በገጠርና በከተማ የትምህርት መሰረተ ልማት ተደራሽነትና ጥራት ማስጠበቅ ላይ በማተኮር እየሰራ ነው።
በአዳማ የተገነባው ትምህርት ቤትም ይህንኑ ተግባር የሚያጠናክር መሆኑን አመልክተዋል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው፥ በከተማዋ የትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻያ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው ፥ በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አዳማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የተገነባው ትምህርት ቤትም አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኮሚሽኑ የአዳማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ መንግስቱ ባልቻ በበኩላቸው፥ ቅርንጫፉ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመሳተፍ የተለያዩ ተግባራት ማከናወኑን ተናግረዋል።
በአዳማ ዳቤ ክፍለ ከተማ ሶሎቄ ዶንጎሬ ወረዳ የከለቾ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገንብተን በዛሬው ዕለት አስረክበናል ብለዋል።