በዞኑ በትምህርት ዘመኑ ለትምህርት ጥራት መጠበቅ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በትምህርት ዘመኑ ለትምህርት ጥራት መጠበቅ ትኩረት ተሰጥቷል

ነቀምቴ፤ጥቅምት 2/2018(ኢዜአ)፦በምስራቅ ወለጋ ዞን በትምህርት ዘመኑ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ትኩረት መሰጠቱን የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ ዘላለም አለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ በዞኑ በትምህርት ዘመኑ ከ450 ሺህ በላይ ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርት ጀምረዋል።
በክረምት ወራት የትምህርት ተደራሽነትና ጥራትን ለማረጋገጥም የሚያግዙ 80 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ለአገልግሎት መብቃታቸውን ተናግረዋል።
ከዚህም ባለፈ አራት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ለ2018 የትምህርት ዘመን አገልግሎት መጀመራቸውን ገልጸዋል።
ከአዳዲስ የትምህርት ቤቶች ግንባታ ጎን ለጎን ነባር ትምህርት ቤቶችን የመጠገንና በትምህርት ቤቶች 460 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች የመገንባት ሥራ መከናወኑን አመልክተዋል።
የመማር ማስተማር ሥራውን ምቹ ለማድረግም ግብአት ከማሟላት በተጨማሪ የትምህርት ምድረ ግቢ ውበት ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈ 81 ሺህ ተማሪዎችን በትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አመልክተዋል።
በትምህርት ዘመኑ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ከግብአት በተጨማሪ ለመምህራንን ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱንም አክለዋል።
ጊዜውን በአግባቡ በመጠቀም ለተሻለ ውጤት እንደሚተጋ የገለጸው ደግሞ በዞኑ የቢፍቱ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የአብስራ ታደሰ ነው።
ሌላኛው ተማሪ ናኦል ደሳለኝ በበኩሉ፥ከመምህራን እገዛ በተጨማሪ ጊዜውን በቤተ መጻህፍት በማሳለፍ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ከወዲሁ ተግቶ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል።