በደሴ ከተማ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የተገኘው ውጤት በበጋው ወራት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በደሴ ከተማ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የተገኘው ውጤት በበጋው ወራት ተጠናክሮ ይቀጥላል

ደሴ፤ ጥቅምት 2/2018(ኢዜአ)፡- በደሴ ከተማ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የተገኘው አበረታች ውጤት በበጋው ወራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የከተማው አስተዳደር አስታወቀ።
የከተማ አስተዳደሩ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ማጠቃለያና የበጋ ወቅት የአገልግሎቱ ማስጀመሪያ መድረክ ተካሂዷል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የደሴ ከተማ ማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰይድ የሱፍ እንደገለጹት፣ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሕብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እየፈታ ነው።
በክረምት ወቅት በተተገበረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካሞችን ቤት መስራት፣ የተቸገሩ ቤተሰቦችን በመደገፍ፣ ማዕድ በማጋራት፣ ጎርፍ በመከላከል፣ በትምህርትና በጤናው ዘርፍ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
የተመዘገበውን ውጤትና የተፈጠረውን ከፍተኛ መነቃቃት በማጠናከር በበጋው ወራት ተግባሩ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰይድ አራጋው በበኩላቸው እንደገለጹት፣ በክረምቱ ከ133 ሺህ በላይ በጎ ፍቃደኞችን በማሳተፍ ከ128 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
በተግባሩም የ336 የአቅመ ደካማ ቤቶች አዲስ ግንባታና ጥገና፣ ችግኝ ተከላ፣ 2 ሺህ 990 የኒት ደም ልገሳና ሌሎችም አገልግሎቶች ተሰጥተዋል ብለዋል።
በበጎ ፈቃድ ስራው በህዝብና በመንግስት ይወጣ የነበረውን በርካታ ገንዘብ ማዳን መቻሉን ጠቁመው የተገኘውን ልምድና ተሞክሮ በመጠቀም በበጋው ወራትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በበጋ በጎ ፍቃድ አገልግሎትም ከ39 ሺህ በላይ በጎ ፍቃደኞችን በማሳተፍ ከ40 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።
በደሴ ከተማ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የተሳተፈችው ወጣት ሰናይት ምትኩ በሰጠችው አስተያየት፣ በክረምቱ የአቅመ ደካሞችን ቤት በመስራት፣ ደም በመለገስ፣ በከተማ ጽዳትና ውበት ተሳትፎ አድርጋለች።
በዚህም የሕብረተሰቡን ችግር ማቃለል መቻላቸውን ጠቁማ በበጋው በጎ ፍቃድ አገልግሎት በመሳተፍ ሕብረተሰቡን ለማገልገል መዘጋጀቷን ተናግራለች።
ሕብረተሰቡን በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በማገልገል የሕሊና እርካታ ማግኘቱን የገለጸው ደግሞ ወጣት ሰይድ አህመድ ነው።
ከሌሎች ጓደኞቼ ጋር በመሆን በአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታ፣ በጎርፍ መከላከል፣ በደም ልገሳ፣ በማካካሻ ትምህርትና በሌሎችም በክረምት በጎ ፍቃድ ያሳየነውን ተሳትፎ በበጋው ወራትም አጠናክረን እንቀጥላለን ብሏል።
በመድረኩ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ በጎ ፍቃደኞችና ሌሎችም የተገኙ ሲሆን የተሻለ አስተዋጽኦ ላበረከቱ በጎ ፍቃደኞች፣ ተቋማትና ግለሰቦች እውቅና ተሰጥቷል፡፡