ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ትግበራ ሀገራዊ ምርታማነትን ለማሳደግ ገንቢ ሚና ይጫወታሉ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 2/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ትግበራ ሀገራዊ የምርታማነት አቅምን ለማሳደግ ገንቢ ሚና  እንደሚጫወቱ የተለያየ ዘርፍ አምራች ኢንዱስትሪዎች ገለጹ።

የስንዴ አምራችና ላኪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ሚሊዮን ቦጋለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ እየተካሔዱ ያሉ ግዙፍ የልማት ስራዎች ለአምራች ኢንዱስትሪው ተጨማሪ አቅም የፈጠሩ ናቸው።

በተለይም ባለፉት የለውጥ ዓመታት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ጨምሮ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ምርታማነት መጨመር የሚያስችል የአሰራር ስርዓት መዘርጋቱ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

በተጨማሪም በመሰረተ ልማት፣በኃይል አቅርቦት፣በግብዓትና በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትም እንዲሁ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ ማንሰራራት አይነተኛ ሚና አላቸው ብለዋል።

በተለይም በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ለግብርና ምርታማነት ትልቅ እድል ይዞ የሚመጣ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ እየተገኘ ያለውን ስኬት በእጥፉ ለማሳደግና በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ከዳር ለማድረስ አይነተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የአፈር ማዳበሪያን ከውጭ ለማስገባት ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ በአገር ውስጥ መተካት የሚያስችል መሆኑ ለኢኮኖሚው እድገት ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መሰረታዊ ብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ስራ አስኪያጅ ሰለሞን ሙሉጌታ በበኩላቸው፤ እንደ ሀገር ተግባራዊ የተደረጉ ፕሮጀክቶች ለአምራች ዘርፉ ምርታማነት ትልቅ እድል ይዘው የመጡ ናቸው። 

ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ የሚሆን በቂ የብረታብረት ግብዓትን ለማቅረብ ተጨማሪ የማምረት አቅምን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

መንግስት በኢንዱስትሪ ዘርፍ በስፋት የሚፈለገውን የሃይል አቅርቦት ለማሟላትና አማራጭ የሃይል አቅርቦትን ለመጨመር የሚያደርገው ጥረት በእጅጉ የሚበረታታ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም በቅርቡ የተመረቁት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ የመጀመሪያ ዙር ፕሮጀክቶች ለብረታብረት ኢንዱስትሪዎች ተጨማሪ የሃይል አቅርቦትን የሚሰጡና ትልቅ ጠቀሜታ ያላቸው መሆናቸውን አንስተዋል።

ይህም ለአገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው ብለዋል። 

የማሽነሪ አምራቾች ማህበር ሊቀመንበር አክሊሉ አባተ እንዲሁ በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ የልማት ስራዎች የአመራር ብቃትና ቁርጠኝነትን በተግባር ያሳዩ ናቸው ብለዋል።

ቀደም ሲል እንደ ሀገር በሃይል እጥረት ምክንያት ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅማቸው ዝቅተኛ እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ መሻሻሎች እንዳሉ አንስተዋል።

ይህም የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም እንዲጨምር እድል የፈጠረና ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንዲያጎላ አስቸሏል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ የተደረጉ ግዙፍ ፐሮጀክቶችን ጨምሮ መሰረት የተቀመጠላቸው ፕሮጀክቶች የኢንዱስትሪዎችን ጫና በማቃለል ረገድ አይነተኛ ሚና አላቸው ብለዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም