ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የዓለም ዋንጫ የመጨረሻ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዋን ከቡርኪናፋሶ ጋር ዛሬ ታደርጋለች

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 2/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ዛሬ ከቡርኪናፋሶ ጋር ትጫወታለች።

የሀገራቱ ጨዋታ በኦገስት 4 ስታዲየም ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ ይደረጋል።

በምድብ አንድ የምትገኘው ኢትዮጵያ በዘጠኝ ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከቀናት በፊት ከጊኒ ቢሳው ጋር ባደረገው የማጣሪያ መርሃ ግብር 1 ለ 0 በማሸነፍ በምድቡ ሁለተኛ ድሉን ማስመዝገቡ ይታወቃል።

በብራማ ትራኦሬ የሚሰለጥነው የቡርኪናፋሶ ብሄራዊ ቡድን ከቀናት በፊት ከሴራሊዮን ጋር ባደረገው ጨዋታ 1 ለ 0 አሸንፏል። ቡድኑ ነጥቡን ወደ 18 ከፍ በማድረግ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

ሁለቱ ሀገራት በዚሁ ምድብ ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ቡርኪናፋሶ 3 ለ 0 ማሸነፏ የሚታወስ ነው።

ሀገራቱ ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው አምስት የእርስ በእርስ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ አንድ ጊዜ ስታሸንፍ ቡርኪናፋሶ ሶስት ጊዜ ድል ቀንቷታል። አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ቡርኪናፋሶ 12 ግቦችን ከመረብ ላይ ስታሳርፍ ኢትዮጵያ ሶስት ግቦችን አስቆጥራለች።

ከዓለም ዋንጫ ውድድር ውጪ ለሆነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የዛሬው ጨዋታ የማጣሪያ ጉዞውን በድል ለመደምደም ያስችለዋል።

ቡርኪናፋሶ ማሸነፍ ከቻለች ለዓለም ዋንጫው ለማለፍ በሚደረገው የጥሎ ማለፍ ውድድር ለመሳተፍ የሚያስችላትን እድል ታሰፋለች።

በዚሁ ምድብ የምትገኘው ግብጽ በ23 ነጥብ ለዓለም ዋንጫ በቀጥታ ማለፏ የሚታወስ ነው።

በምድብ አንድ ግብጽ ከጊኒ ቢሳው፣ ጅቡቲ ከሴራሊዮን ዛሬ በተመሳሳይ ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም