የአፍሪካን የትርክት ሉዓላዊነት እና የሚዲያ ነጻነት የማረጋገጥ ጅማሮ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካን የትርክት ሉዓላዊነት እና የሚዲያ ነጻነት የማረጋገጥ ጅማሮ

ለዘመናት የአፍሪካ ታሪክ ሲነገር የቆየው በሌሎች ነው። አህጉሪቱን አስመልክቶ የሚሰሩ ዘገባዎች አፍሪካውያንን በተሳተተ መነጽር የሚመለከቱና ማንነታቸውን የማይወክሉ፣ ትርክቱ አፍሪካን በቀውስ መነጽር ብቻ እንድትሳል የሚያደርጉ ናቸው። ከቅኝ ግዛት ፕሮፓጋንዳ እስከ ዘመናዊ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘገባ የአፍሪካ አብዛኞቹ ትርክቶች የተቀረጹት በውጭ ኃይሎች ነው።
ውጪዎቹ የአፍሪካን እሳቤ እና አጀንዳ የማህበረሰቦችን እሴት፣ ባህል፣ ታሪክ እና የአንድነት መንፈስ በውል ያልተረዱ ናቸው። ዓለም ስለአፍሪካ ሁሌም የሚያዳምጠው ስለጦርነት፣ ስለድህንት እና ስለአህጉሪቱ ፈተናዎች ነው። ምልከታዎቹ የአፍሪካ ፈጣሪዎችን፣ ልሂቃንን ህልመኞችን፣ የኪነ ጥበብ ሰዎችንና ስኬታማ ሰዎችን ያገለሉ መሆናቸው በግልጽ ይታያል።
አፍሪካ ሁሌም የምትበየነው ለመልማት እና ለመበልጸግ ባላት መሻትና አቅም ወየም ለተቀረው ዓለም በምታቀርባቸው መልካም እድሎች ሳይሆን ባጣቻቸው ነገሮች ነው። የዓለም መገናኛ ብዙሃን የአፍሪካ ዘገባዎች ፈተናዎችን ብቻ የሚያጎሉ ናቸው። የዓለም አርዕስተ ዜናዎች የአፍሪካን የመፍጠር አቅም፣ አይበገሬነት እና ለውጥ የሚያንጸባርቁ አይደሉም።
በአህጉሪቱ ያለው ሚዛናዊነት የጎደለው እይታ ከዓለም እይታ ብቻ የሚመነጭ አይደለም። አፍሪካውያን ራሳቸውን የሚመለከቱበትና የሚለኩበት መንገድም የተዛባ በመሆኑም ጭምር ነው።
መረጃ ኃይል በሆነበት በዚህ ዘመን የአፍሪካን እውነተኛ ድምጽ የሚያሰማ ሚዲያ አለመኖር አሉታዊ ተጽእኖዎች ያሉት ነው። የሚዲያ ትርክቶች ፖሊሲ፣ ኢንቨስትመንትና ዲፕሎማሲ ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ከመሆናቸው ባሻገር በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ሀገር ተረካቢ ወጣትን በእሳቤ የሚቀርጹ ናቸው። የአፍሪካ ገጽታ ስቃይ እና ሁሌም ችግር የዓለም መገናኛ ብዙሃን ዘገባ ላይ በገነነበት ወቅት ዓለም አፍሪካን እንደ አጋር ሳይሆን እንደ ርዳታ ጠባቂ አህጉር አድርጎ እንዲመለከታትም ምክንያት ሆኗል።
የዓለም መገናኛ ብዙሃን የአፍሪካን የኢኮኖሚ እድገት፣ የቴክኖሎጂ እምርታ፣ ታሪክ እና ባህል ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ችግርን አብዝተው ማቀንቀናቸው አህጉሪቱ በሚዲያው ዘርፍ ፍትሃዊ ውክልና ሊኖራት ይገባል የሚሉ ድምጾች ጎልተው እንዲሰሙ አድርጓል።
የሚዲያ ውክልናው ጋዜጠኝነት ተኮር ሳይሆን አፍሪካ የማንነቷ ባለቤት እንድትሆን እና የራሷን መጻኢ ዕድል የመወሰን መብቷን እንድታረጋግጥ ያለመ ጥሪ ነው።
እ.አ.አ 2022 35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የተካሄደበት ወቅት ነው። የአፍሪካ መሪዎች በአህጉራዊ አጀንዳዎች ላይ ለመምከር በአዲስ አበባ ተገኝተዋል። በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ያደረጉት ንግግር በርካታ የአፍሪካ አጀንዳዎችን ቃኝቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በወቅቱ አፍሪካ የትርክት ነጻነትቷን ማግኘት አለባት በሚል ያነሱት ሀሳብ የጉባኤውን ተሳታፊዎች ቀልብ የሳበ ጉዳይ ነበር። ለዘመናት የአፍሪካ ምስል የተቀረጸው በውጭ ኃይሎች እንደሆነ አንስተው የትርክት ቅኝቱ አህጉሪቱ የድህነት፣ የግጭት እና የተረጂነት ምሳሌ አድርጎ የሚያቀርብ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ አፍሪካውያን የአህጉሪቱን ብዝሃነት፣ አይበገሬነት እና የኢኖቬሽን አቅም የሚያሳዩ ሀገር በቀል የኮሙኒኬሽን አማራጮች ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ ማቅረባቸውም ይታወሳል።
አፍሪካ የራሷን ጉዳይ በራሷ አፍ የምትናገርበት አህጉራዊ የፖን አፍሪካ ሚዲያ እንዲቋቋም ሀሳብ አቅርበው እንደነበርም እንዲሁ። ይህ ሀሳብ በጉባኤው ተሳታፊዎች ከፍተኛ ድጋፍ አገኝቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) Pulse of Africa የተሰኘ የፓን አፍሪካ ሚዲያ በያዝነው ሳምንት በይፋ አስጀምረዋል። ሚዲያው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እ.ኤአ በ2022 በ35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የአፍሪካን እይታ እና ትርክት የሚያንፀባርቅ የአኅጉራዊ ሚዲያን አስፈላጊነት አስመልክተው ያቀረቡትን ጥሪ በመመርኮዝ የተመሠረተ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
Pulse of Africa የአፍሪካን ድምፆች የሚያጎላ፣ ቀጠናዊ ትስስርን የሚያጠናክር እና አኅጉራዊ ስኬቶችን፣ ተግዳሮቶችን እና ሕልሞችን በአፍሪካዊ እይታ የሚገልጥ ሚዲያ የመሆን አላማ አለው። በዚህም Pulse of Africa ሚዲያ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ እና ህልም ቀጥተኛ ምላሽ የሰጠ ሆኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በፓን አፍሪካ ሚዲያው ምርቃት ላይ ባደረጉት ንግግር አፍሪካ ትልቅ ሳለች ትንሽ መስላ እንድትታይ ያደረጋት ዋነኛ ምክንያት የአፍሪካ ሀገራት በትርክት ጭንቅላትን የመመገብ ዝግጁነት ውስን በመሆኑ ነው ብለዋል።
የPulse of Africa ሚዲያ በጥቂት ዓመታት በአፍሪካ ቀደምት እና ታዋቂ ከሆኑ ሚዲያዎች አንዱ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም ሲሉም ነው የተናገሩት። የአንድ ሀገር ሚዲያ እድገት ከሀገራት ኢኮኖሚ እና እድገት ጋር የተሳሰረ መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያ በማንሰራራት ላይ እንደምትገኝ አመልክተዋል።
የዛሬ 10 ዓመት የምትኖረው ኢትዮጵያ በአፍሪካ በብዙ ነገር ግንባር ቀደም ትሆናለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያኔ ትርክት መገንባት የመሻት ጉዳይ ሳይሆን የኃላፊነት ጉዳይ መሆኑንም ነው ያነሱት። ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዋ እያደገ ሲሄድ በአፍሪካ ትርክት ውስጥ ጉልህ ስፍራ መጫወት ኃላፊነቷ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ከራሷ በመሻገር የአፍሪካን ትልቅነት፣ ሀብታምነት፣ የማድረግ አቅም እንዲሁም አፍሪካውያን ሲደመሩ የተሻለ ነገር ማምጣት እንደሚችሉ የPulse of Africa ሚዲያ በብዙ ነገር እንደሚያስተምርም ተናግረዋል።
Pulse of Africa የአፍሪካ ድምጽ ነው፤ የአፍሪካ ምስል፣ ባህል እና ሀብት መገለጫ መሆኑንና ከአፍሪካ ወንድሞቻችን ጋር በሁሉም ነገር በትብብርና በመደመር በጋራ መቆም ይገባናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ረገድም Pulse of Africa የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ማሳሰባቸው ይታወሳል።
Pulse of Africa ሚዲያ ጋዜጠኞች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እና ታሪክ ነጋሪዎችን ጨምሮ አፍሪካውያን ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች በማገናኘት የአፍሪካን እውነተኛ መልክ ለማሳየት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣና የአፍሪካን ትርክት መገንባት፣ ብዝሃነት በማንጸባረቅ እና የአፍሪካን እውነተኛ ታሪክ በአህጉራዊ መነጽር ለመቃኘት የሚያስችል ነው።
Pulse of Africa ከሚዲያ ኢኒሼቲቭ ባለፈ አፍሪካ ራሷን በራሷ መበየን የምትችልበት አዲስ ምዕራፍ እንደሆነ ብሎ መውሰድ እንደሚቻልና አህጉሪቱ እውነቷን እንድትናገርና በዓለም መድረክ ተገቢውን ክብር እንድታገኝ የማድረግ ጉዞ አካል ነው። ሚዲያው ዜናን ከመዘገብ ባለፈ አፍሪካ የራሷን ታሪክ በራሷ ቃና እና ድምጽ እንድትናገር ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱም ተመላክቷል።