የአርሶ አደሩን ህይወት በመቀየር በኢትዮጵያ የሚታሰበውን ለውጥ ማምጣት ይቻላል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የአርሶ አደሩን ህይወት በመቀየር በኢትዮጵያ የሚታሰበውን ለውጥ ማምጣት ይቻላል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2018(ኢዜአ)፦ የአርሶ አደሩን ህይወት በመቀየር በኢትዮጵያ የሚታሰበውን ለውጥ እውን ማድረግ እንደሚቻል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከፌዴራል እና ከክልል አመራሮች ጋር የገጠር ኮሪደር ስራዎች ላይ ውይይት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የገጠር ኮሪደር ስራው ገጠርን የማሻገር እና የገጠሩን አርሶ አደር ህይወት የማዘመን አላማ ያነገበ መሆኑን ገልጸዋል።
በሀላባ፣ ከምባታ፣ ሀዲያ እና ስልጤ ዞኖች የተሰሩት የሞዴል ገጠር መንደሮች ከፍተኛ ደስታን እንደሚፈጥሩም ተናግረዋል።
የእያንዳንዱን አርሶ አደር ህይወት መቀየር ከተቻለ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እና በብዙ መልኩ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ያግዛል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ያለውን የመቀንጨር ችግር መቅረፍ የሚያስችሉ እንቁላል፣ ማር፣ ስጋ፣ ዶሮ፣ ፍራፍሬ፣ ጎመን እና ሰላጣን ጨምሮ በየጓሮው የሚለሙ በቂ ንጥረ ነገር ያላቸው ምግቦች እንዳሉ አንስተዋል።
እነዚህን እየተመገበ ያደገ ሰው ሊቀነጭርና ሊራብ አይችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የገጠር ኮሪደር ስራ መቀንጨርን ለመከላከል እንደሚያግዝም አመልክተዋል።
በዚህም የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እና ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚቻል ነው ያነሱት።
የገጠር ኮሪደር ስራን ለማስፋትና ለማጠናከር የጋራ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ይህን ኢኒሼቲቭ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ማስፋት ከተቻለ በኢትዮጵያ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አመልክተዋል።
የአርሶ አደሩን ኑሮ መቀየር መቻሉ አስደሳች መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ መልካም ጅማሮ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።