ቀጥታ፡

የጋራና የውክልና ገቢ አሰባሰብ ውጤታማ አፈጻጸም ፍትሐዊ የመሰረተ ልማት ሥርጭት እውን እንዲሆን እያደረገ ነው  

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2018 (ኢዜአ)፡-የፌደራልና ክልል መንግስታት የጋራና የውክልና ገቢ አሰባሰብ ውጤታማ አፈጻጸም ፍትሐዊ የመሰረተ ልማት ሥርጭት እውን እንዲሆን እያደረገ እንደሚገኝ የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ ገለጹ።

የገቢዎች ሚኒስቴር ከፌዴራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር የገቢ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ከመስከረም 29 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ሲያካሂድ የቆየውን የውይይት መድረክ አጠናቋል።


 

የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የወሰደችው የፖሊሲ ለውጥና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በገቢ አስተዳደር ስርዓቱ ላይ እመርታዊ ለውጥ እንዲመዘገብ እያደረገ ነው።

በዚህም ሀገራዊ ወጪን በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችል የታክስ አስተዳደር አቅም በመገንባት ረገድ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።

የታክስ አስተዳደር ሥርዓቱ ለፌዴራል መንግስት፣ ለክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሰጠው ግልጽ የተግባርና ኃለፊነት እርከን መኖሩን አስረድተዋል።

ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር በተፈጠረ ተግባቦትም የኢትዮጵያን የታክስ አስተዳደር ውጤታማና ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ ማስቀጠል የሚያስችል ምኅዳር መፈጠሩን ተናግረዋል። 

በዚህም በጋራና የውክልና ገቢ አሰባሰብ ላይ የተፈጠረው የተሻለ አፈፃጸም በሁሉም አካባቢዎች ላይ ፍትሐዊ የመሰረተ ልማት ሥርጭት እንዲረጋገጥ እያደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።


 

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የተወሰደው የማሻሻያ እርምጃም የፌዴራልና የክልል መንግስታትን እንዲሁም የከተማ አስተዳደሮችን የገቢ መሰብሰብ አቅም በማጎልበት ገንቢ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አስረድተዋል።

በ2018 በጀት ዓመት የተያዘውን ሀገራዊ የገቢ ዕቅድ ለማሳካት፣ ዘላቂ የገቢ ዕድገትን ለማረጋገጥና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከክልሎች ጋር በጋራ ለመስራት በውይይት መድረኩ መግባባት ላይ መደረሱን አንስተዋል።

ሀገራዊ የልማት ስራዎችን ለማሳካት ሙሉ አቅምን መጠቀምና ቅንጅታዊ ስራዎችን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል። 

ፍትሐዊ የታክስ አስተዳደር ስርዓት ለመዘርጋት የታክስ አወሳሰንና ሌሎች ስራዎችን ለማጎልበት የግንኙነት ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም