የኢትዮጵያውያን ባህላዊ ምግቦች በርካታ አዳዲስ የኢኮኖሚ ሃብት መፍጠር የሚችሉ እሴቶች ናቸው - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያውያን ባህላዊ ምግቦች በርካታ አዳዲስ የኢኮኖሚ ሃብት መፍጠር የሚችሉ እሴቶች ናቸው - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያውያን ባህላዊ ምግቦች በርካታ አዳዲስ የኢኮኖሚ ሃብት መፍጠር የሚችሉ እሴቶች መሆናቸውን የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
በቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩትና ኩሪፍቱ ሪዞርት የአፍሪካ መንደር ትብብር የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦች ፌስቲቫል መካሄድ ጀምሯል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚህ ወቅት፥ ፌስቲቫሉ የኢትዮጵያውያንን ባህላዊ ምግብና መጠጦች ለማስተዋወቅ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው ብለዋል።
በክህሎት ልማትና በሥራ ዕድል ፈጠራ የኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌትነት የሚያረጋግጡ ወሳኝ ስኬቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያውያን ባህላዊ ምግቦች በርካታ አዳዲስ የኢኮኖሚ ሃብት መፍጠር የሚችሉ እሴቶች መሆናቸውን አንስተዋል።
ባህላዊ ምግቦቻችን የኢትዮጵያን መልከብዙነት የሚገልጡ የህብረ ብሔራዊነታችን እሴቶች ናቸው ያሉት ሚኒስትሯ፥ እነዚህን ሃብቶች በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የገቢ ምንጭና የስራ ዕድል መፍጠሪያ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ፥ ኢትዮጵያ በዘላቂነት ከቱሪዝም ተጠቃሚ መሆን የምትችልባቸው ጸጋዎች ባለቤት ናት ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብና መጠጦች ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እንዲተዋወቁ የጥናትና ምርምር እንዲሁም ሙያዊ የማማከር ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በጥናት የተለዩ የኢትዮጵያውያን ባህላዊ ምግብና መጠጦች በኩሪፍቱ አፍሪካ ቪሌጅ መቅረባቸውን ገልጸዋል።
የኩሪፍቱ ሪዞርቶች ባለቤት አቶ ታድዮስ ጌታቸው÷ የኩሪፍቱ አፍሪካ መንደር የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦችን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እያስተዋወቀ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የአማራ ክልልን በመወከል የባህል ምግቦችን በፌስቲቫሉ ያቀረቡት ብዙአየሁ ሞላ÷ የምግብ ፌስቲቫሉ የብሔር ብሔረሰቦችን ባህላዊ የምግብ ሥርዓት ለማስተዋወቅ ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።
የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልልን በመወከል የባህል ምግቦችን ያቀረቡት መልሔት ሐሚት በበኩላቸው÷ ብሔር ብሔረሰቦችን አንዱ የሌላውን የባህል ምግብ አሰራርና አዘገጃጀት እንዲያውቅ መልካም ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
በሀድያ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የባህልና ቅርስ ባለሙያ ትዕግስት ገብረየሱስ÷ በፌስቲቫሉ ለሰው ልጅ ጤና ተስማሚ ባህላዊ ምግቦችን በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እያስተዋወቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የስልጤ ዞን ባህልና ቱሪዝም ኃላፊ ይርዳው ናስር (ዶ/ር)÷ የባህል ምግቦች ላይ ጥናት በማካሄድ በኤግዚቢሽን መልክ የማስተዋወቅ ስራው ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት የኢኮኖሚ አቅም መሆኑን ገልጸዋል።
ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የም ዞን የመጡት ጸሐይነሽ ገብረማርያም÷ በብሔረሰቡ የሚዘወተሩ ጠቃሚ የምግብ አይነቶችን በፌስቲቫሉ በማቅረብ የማስተዋወቅ ስራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በፌስቲቫሉ ላይ ከሁሉም ክልሎች ለማሳያነት የተመረጡ የ31 ብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ ምግቦች ቀርበዋል።
ፌስቲቫሉ ባህላዊ ምግቦችን በማስተዋወቅ ወደ ገበታ እንዲመጡ ማድረግ፣ የእርስ በርስ ትውውቅን መፍጠር፣ የሀገር ገጽታ መገንባትና የምግብ ቱሪዝምን ለማሳደግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።