ሀገርን የሚያሻግሩ ትልልቅ የዲጂታል ኢኒሼቲቮችን የሳይበር ደህንነት ማረጋገጥ ዋነኛ ትኩረት መሆን አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ሀገርን የሚያሻግሩ ትልልቅ የዲጂታል ኢኒሼቲቮችን የሳይበር ደህንነት ማረጋገጥ ዋነኛ ትኩረት መሆን አለበት

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2018 (ኢዜአ)፡-ሀገርን የሚያሻግሩ ዲጂታል የልማትና የአገልግሎት ኢኒሼቲቮችን ለማሳካት የሳይበር ደህንነትን ማረጋገጥ ዋነኛ የትኩረት ማዕከል መሆን እንዳለበት የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለም ፀሐይ ጳውሎስ ገለፁ።
ከዛሬ ጥቅምት 1 ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆየው ስድስተኛው አገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር የማስጀመሪያ መረሃ-ግብር በአዲስ አበባ ተካሒዷል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሐይ ጳውሎስ ባስተላለፉት መልዕክት ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሁሉም ዘርፎች ስኬታማ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል።
የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጅማሮ ማሳያ የሆኑ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የተመረቁና የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መንግስት ለዘላቂ ልማትና እድገት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳዩ ናቸው ብለዋል።
የዜጎችን የዕለት ተዕለት የህይወት እንቅስቃሴና የመንግሥትን አገልግሎት የሚያሳልጡ የዲጂታል አሠራሮችን በመተግበር ተጨባጭ ለውጦች መምጣታቸውን አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ900 በላይ የሚሆኑና በተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ አማካይነት ለተገልጋዮች ተደራሽ እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ቴክኖሎጂና ልማት ተሰናስለው የሚሔዱ ናቸው ያሉት ሚኒስትሯ፤ የልማት ስራዎቹ ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲቆይ ማድረግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።
የሳይበር ደህንነት ጉዳይ ከሀገር ሉዓላዊነት ጋር የሚተሳሰር በመሆኑ በዘርፉ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ለዚህም በተለያዩ አማራጮች ተደራሽ የሚደረጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ጉልህ ሚና እንዳላቸው ነው የጠቆሙት።
የሳይበር ደህንነት ወር እንደ ሀገር በሳይበር ደህንነት ላይ የሚከናወኑ ተግባራትን በስፋት ለማስገንዘብ እድል የሚፈጥርና የተቋማትን ቅንጅታዊ አሰራር ለማጠናከር የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ስለሆነም በመላ ሀገሪቱ በሳይበር ደህንነት ዙሪያ የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ በሆነ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ በበኩላቸው፤ ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ የተከናወኑ የልማት ስራዎች፣ ተገንብተው የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችና የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሀገሪቷን ኢኮኖሚያዊና ሁሉን አቀፍ እድገት የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።
እነዚህና ሌሎች የልማት ስራዎች ለዘላቂ ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ እድገት ያላቸውን ፋይዳ ለማጉላት ደህንነታቸውን በአግባቡ ጠብቆ ማቆየት የግድ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ለዚህም የሳይበር ደህንነት ጉዳይን ወጥነት ባለው መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ ስለመሆኑ አንስተዋል።
ለአብነትም በየዓመቱ የሚከበረው የሳይበር ደህንነት ወር የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ-ግብር አንዱና ዋነኛው መሆኑን አስረድተዋል።
በእነዚህና ሌሎች የቅድመ መከላከል ስራዎች በተከናወኑ ተግባራት የሳይበር ጥቃት ምጣኔን መቀነስ ተችሏል ነው ያሉት።
የዘንድሮው የሳይበር ደህንነት ወር "የሳይበር ደህንነት የዲጂታል ኢትዮጵያ መሰረት” በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሔድ ይሆናል፡፡