ቀጥታ፡

የ2017 ሀገራዊ የመጅሊስ ምርጫ በለውጡ መንግስት የተገኘ ታሪካዊ ስኬት ነው - ሸህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የ2017 ሀገራዊ የመጅሊስ ምርጫ በለውጡ መንግስት የተገኘ ታሪካዊ ስኬት ነው ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ገለፁ።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የ2017 ሀገራዊ የመጅሊስ ምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ የምርጫውን መጠናቀቅ ምክንያት በማድረግ የዕውቅናና ምሥጋና መርሐ ግብር አካሂዷል። 


 

በመርሐ ግብሩ ቦርዱ ለምርጫው ስኬታማነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እውቅናና ምስጋና ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ምርጫው በለውጡ መንግስት የተገኘ ታሪካዊ ስኬት ነው።

የመጅሊሱ ምርጫ ጠንካራና ዘላቂ ኢስላማዊ ተቋም ለመፍጠር ያለመ እንደነበር ገልጸው፤ የተጠናቀቀው ሂደት የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን አንድነት ያሳየ መሆኑን አብራርተዋል።

ፕሬዝዳንቱ ምርጫው ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ትልቅ ድርሻ ላበረከተው መንግስት ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፤ ህዝበ ሙስሊሙ በምርጫው ላደረገው ተሳትፎም አመስግነዋል።


 

ፍትሃዊና ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሁሉ ምስጋና ይገባል ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የ2017 የመጅሊስ ምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ ሰብሳቢ አብዱላዚዝ ኢብራሂም (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ከፌዴራል እስከ መስጂድ የተዋቀረው የምርጫ አስፈፃሚ ተቋማዊ ተልዕኮውን በስኬት አጠናቋል።


 

ምርጫው መላውን ህዝበ ሙስሊም ከጫፍ እስከ ጫፍ አሳትፎ በስኬት የተጠናቀቀ ሲሆን፤ በቀጣይ ለሚደረጉ ምርጫዎችም ትምህርት የተወሰደበት መሆኑን ገልጸዋል።

በመጨረሻም የመጅሊሱ ምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ አመራር አባላት በምርጫው ሂደት ውስጥ ለተሳተፉና ስኬታማ እንዲሆኑ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም