በጤናው ዘርፍ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት እየተደረጉ ባሉ ሁሉን አቀፍ ጥረቶች አበረታች ውጤት ተመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
በጤናው ዘርፍ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት እየተደረጉ ባሉ ሁሉን አቀፍ ጥረቶች አበረታች ውጤት ተመዝግቧል

ባሕርዳር፤ ጥቅምት 1/2018(ኢዜአ)፡- በጤናው ዘርፍ የተቀመጡ የልማት ግቦችን ለማሳካት በክልሉ እየተደረጉ ባሉ ሁሉን አቀፍ ጥረቶች አበረታች ውጤት መመዝገቡን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በጤናው ዘርፍ እያከናወኑት ባሉት ተግባራት ዙሪያ ዛሬ በባሕርዳር ከተማ የምክክር መድረክ አካሄዷል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ መልካሙ ጌትነት በመድረኩ ላይ እንዳመለከቱት፤ እንደሀገር በጤናው ዘርፍ የተቀመጡ የልማት ግቦችን ለማሳካት ክልሉ የድርሻውን እየተወጣ ነው ።
በዚህም እየተደረጉ ባሉ ሁሉን አቀፍ ጥረቶች አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸው፤ በዚህም ተላላፊ በሽታዎች እየቀነሱ እና የእናቶችና ህፃናት ጤና እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
የክልሉ የጤና ስርዓት እንዲሻሻልና በተላላፊ በሽታዎች መቀነስ ለተገኘው ውጤት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አንስተዋል።
በመሆኑም ጤናማና አምራች ዜጋን ለመፍጠር ቢሮው ከአጋር አካላት ጋር የጀመረውን ቅንጅታዊ አሰራር ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።ቢሮው የ25 ዓመት የጤናው ዘርፍ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱም ተመልክቷል።
የመድረኩ ተሳታፊ አጋር አካላት ለክልሉ የጤና ዘርፍ ውጤታማነት ሲያደርጉት የቆየውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ የጤና ቢሮ አመራሮችና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የሰቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተሳትፈዋል።