በሀዋሳ ከተማ የህብረተሰቡን ህይወት የሚያሻሽሉ የልማት ስራዎች በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላሉ-ከንቲባ ተክሌ ጆንባ - ኢዜአ አማርኛ
በሀዋሳ ከተማ የህብረተሰቡን ህይወት የሚያሻሽሉ የልማት ስራዎች በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላሉ-ከንቲባ ተክሌ ጆንባ

ሀዋሳ ፤ ጥቅምት 1/2018(ኢዜአ)፦ በሀዋሳ ከተማ የህብረተሰቡን ህይወት የሚያሻሽሉ የልማት ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥሉ የከተማዋ ከንቲባ ተክሌ ጆንባ ተናገሩ።
የሀዋሳ ከተማ ምክር ቤት 2ኛ ዙር 10ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ጉባኤውን ያካሄደ ሲሆን በጉባኤውም የከንቲባ ተክሌ ጆንባን ሹመት በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡
ከሹመቱ በኋላ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ ተክሌ በሥራ ዘመናቸው የከተማዋን ነዋሪ ህይወት የሚያሻሽሉ የልማት ስራዎች በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላሉ ብለዋል።
በተለይ የድህነት ቅነሳና ሰው ተኮር ልማት ሥራዎች በልዩ ትኩረት እንደሚከናወኑ ገልጸው የከተማ ግብርናና የሌማት ትሩፋት እንዲሁም የማህበራዊ ልማት ስራዎች ትኩረት ይሰጣቸዋል ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ የከተማዋ ወጣቶች ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን ሙያዊ ክህሎት እንዲጨብጡና የሥራ ዕድል እንዲመቻችላቸው ይሰራል ብለዋል፡፡
የከተማዋን ሠላምና ፀጥታ ጠብቆ ማስቀጠል እንዲሁም ዘመናዊ አገልግሎት አሰጣጥና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ማድረግ የከተማ አስተዳደሩ የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
የከተማዋን የቱሪስት መዳረሻዎች ማዘመንና መንከባከብ ብሎም ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ማድረግም ቀጣዩ ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ምክር ቤቱ በጉባኤው በከንቲባ አቶ ተክሌ ጆንባ የቀረቡለትን ሹመቶችም ያጸደቀ ሲሆን ኢንጂነር ቸርነት ፍላቴ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ፣ አቶ ገዛኸኝ አርሲቻ የመሬት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ፣ አቶ ስጦታው ከንባታ የግብርና መምሪያ ኃላፊ እንዲሁም አቶ ገነነ ገላሳ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል፡፡