በድሬዳዋ አስተዳደር የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እውቅና እና ሽልማት ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ አስተዳደር የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እውቅና እና ሽልማት ተሰጠ

ድሬደዋ፤ ጥቅምት 1/2018(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ አስተዳደር በ2017 ዓ.ም የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እውቅና እና ሽልማት ተሰጠ።
በእውቅናና ሽልማት መርሃ ግብሩ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፤ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልይ እና ሌሎች የአስተዳደሩ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በዚህም በ2017 ዓ.ም የ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን 574 በማምጣት ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበችው ተማሪ አፎሚያ ጋሹ ከ250 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ የኤሌክትሮኒክስ ቁሶችና 45 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶለታል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በወቅቱ እንደተናገሩት፤ አምና ለተመዘገበው የተሻለ ውጤት የመምህራንና የወላጆች የተቀናጀ ድጋፍና ክትትል እንዲሁም በትምህርት ዘርፍ የተሰሩ የለውጥ ስራዎች ማሳያ ናቸው።
አስተዳደሩ ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ወላጆች ከመምህራንና ትምህርት ቤቶች ጋር የጀመሩትን የድጋፍና የክትትል ስራዎች በማጠናከር የተሻለ ውጤት እንዲመጣ መትጋት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ተሸላሚዎች በቀጣይም ትምህርታቸውን በትጋት በመከታተልና ውጤታማ በመሆን ሃገርን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ መስራት እንዳለባቸው አስታውሰዋል።
ከተሸላሚዎቹ መካከል የተማሪ አፎሚያ አባት አቶ ጋሹ ሙሉ እንዳሉት፤ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ የወላጅ ድጋፍና ክትትል መሰረታዊ ጉዳይ ነው ።
"እኛ በቤት ውስጥ ከምናደርገው ድጋፍ ባሻገር ከትምህርት ቤቶች ጋር በመቀናጀት ያደረግነው ክትትል ጥሩ የሚባል ነው'' ሲሉ ተናግረዋል።
በ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና 543 በማስመዝገብ ተሸላሚ የሆነው ተማሪ አቡበከር ካሊድ እና በማህበራዊ ሳይንስ 500 በማምጣት የተሸለመችው ተማሪ ኤፍራታ ኢሳያስ፣ ሽልማቱ ወደ ፊት የበለጠ ትምህርታቸውን በርትተው እንዲማሩ እና ተተኪዎች እንዲነቃቁ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር በዘንድሮ አመት የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ በተቀናጀ መንገድ እየሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልይ ናቸው።