የገቢ አሰባሰብን በውጤታማነት መምራት ጠንካራ ሀገር የመገንባት ህልማችንን ለማሳካት ወሳኝ ነው - አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
የገቢ አሰባሰብን በውጤታማነት መምራት ጠንካራ ሀገር የመገንባት ህልማችንን ለማሳካት ወሳኝ ነው - አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2018(ኢዜአ)፦ የገቢ አሰባሰብን በውጤታማነት መምራት ሁለንተናዊ ብልፅግናን በማፋጠን ጠንካራ ሀገር የመገንባት ህልማችንን ለማሳካት ወሳኝ ነው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለፁ።
የገቢዎች ሚኒስቴር ከፌዴራል የክልልና የከተማ አስተዳደር የገቢ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ከመስከረም 29 ቀን 2018 ጀምሮ በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ሲያካሂድ የቆየውን የውይይት መድረክ አጠናቋል።
አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በገቢ አሰባሰብ ላይ በተሰሩ ስራዎች ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል።
ለዚህም የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችና የገቢ ተቋማት በዲጂታል የታገዘ የአሠራር ሥርዓት ማሻሻያዎች ጉልህ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል።
ታማኝ የግብር ከፋዮች እየተበራከቱ መምጣታቸው እንዲሁም የአመራሩ ክትትልና ድጋፍ የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻላቸውን አንስተው ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የግብር ከፋዮች የታክስ አከፋፈል እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸው አሁንም በአመለካከት ችግሮች ምክንያት የሚፈጠሩ የታክስ ስወራና ሌሎች ህገወጥ ስራዎችን መታገል ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የታክስ አጣጣልና አሰባሰብ ስርዓት ውጤታማነት ለሀገራዊ ልማት መፋጠን ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው በማንሳት የገቢ ግብር አሰባሰቡን በውጤታማነት መምራት የግድ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅም መፍጠር ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ እንደሚያሳካ ጠቁመው ለዚህ ደግሞ ገቢ የመሰብሰብ አቅምን ማሳደግ ሚናው የላቀ ነው ብለዋል።
የፌደራልና የክልል የገቢ ዘርፍ አመራሮች ተልዕኳቸው ገቢ መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን ተቋምና ሀገር መገንባት መሆኑን አውቀው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም አሳስበዋል።