በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የወባ በሽታን ለመከላከል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የወባ በሽታን ለመከላከል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው

ወላይታ ሶዶ፤ ጥቅምት 1/2018 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የወባ በሽታን ለመከላከልና የህብረተሰቡን ጤንነት ለመጠበቅ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ እንዳሻው ሽብሩ፤ በክልሉ የወባ መከላከልና የህክምና አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ረገድ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በማብራሪያቸውም በክልሉ ለወባ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት በተቀናጀ መልኩ የመከላከል፣ የቁጥጥር፣ ክትትልና ድጋፍ እንዲሁም የህክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ለወባ መራቢያ ምቹ የሆኑ ስፍራዎችን በማጽዳትና ማህበረሰቡም የመከላከያ መንገዶችን እንዲከተል እየተደረገ መሆኑን አንስተው ፤ አሁን ላይ 91 ሺህ ከረጢት ኬሚካል እና 556 ሺህ የአልጋ አጎበሮች ስርጭት መደረጉንም ጠቅሰዋል።
የወባ መከላከሉ ስራ በቅንጅት በመሰራቱ የስርጭት መጠኑ እየቀነሰ ቢሆንም በቀጣይ ብዙ ስራ የሚጠይቅ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
የወላይታ ሶዶ ከተማ ጤና መምሪያ የበሽታ መከላከል ዘርፍ ኃላፊ በረከት ብርሃኑ፤ የወባ ስርጭትን ለመከላከል ከህዝቡና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በወላይታ ሶዶ እና አካባቢው ነዋሪዎችም በባለሙያዎች ምክር፣ አጎበር በመጠቀምና አካባቢዎችን በማጽዳት ጭምር ወባን እየተከላከሉ መሆኑን ተናግረዋል።