ቀጥታ፡

የጀግንነትና አሸናፊነት ምልክት የሆነውን ሰንደቅ አላማ ክብሩን አስጠብቆ ማቆየት የሁሉም ኃላፊነት ነው

ቦንጋ፤ ጥቅምት 1/2018 (ኢዜአ)፡- የጀግንነትና አሸናፊነት ምልክት የሆነውን ሰንደቅ አላማ ክብሩን አስጠብቆ መዝለቅ የሁሉም ሃላፊነትና አደራ መሆኑ ተገለጸ።

የፊታችን ሰኞ የሚከበረውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተመለከተ የኢዜአ ሪፖርተር  በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ በመዘዋወር የፖሊስ አባላትንና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን አነጋግሯል።

የክልሉ ፖሊስ ከፍተኛ መኮንኖች መካከል ዋና ኢንስፔክተር ብርሃኑ አበራ እና ኢንስፔክተር ደጀኔ አሰፋ፤ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከጥንት እስካሁንም የዘለቀ የጀግንነት፣ የአይበገሬነትና የአሸናፊነት ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የሰንደቁን ክብር በመጠበቅ ጸንታ የምትቀጥል ጠንካራ ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ሁሌም ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።

በቦንጋ ከተማ የሚኖሩት አቶ መንገሻ ወልደማሪያም፤ በበኩላቸው የህብረ ብሄራዊ አንድነትና የጀግንነት ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ለቀጣዩ ትውልድ ከነክብሩ ማስረከብ ይገባል ብለዋል።

የቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ መምህር ተስፋዬ ወንድማገኝ፣ሰንደቅ ዓላማ ከትምህርት ቤት ጀምሮ ልዩ ቦታና ክብር ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸው በተለይም ትውልድ የመቅረጽ ሃላፊነት ያለብን መምህራን ልዩ የቤት ስራ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በብሄራዊ ደረጃ የፊታችን ሰኞ "ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ!” በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበር ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም